Search

ኢትዮጵያ የቀጣናዊ የኃይል ትስስርን እና የቴክኖሎጂ አቅምን ለማሳደግ እየሰራች ነው፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ቅዳሜ ጥቅምት 14, 2019 64

ኢትዮጵያ የቀጣናዊ የኃይል ትስስርን እና የቴክኖሎጂ አቅምን ለማሳደግ እየሰራች መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ12ኛው የጣና ፎረም ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን በተመለከተ አፍሪካ የምታመርታቸው ምርቶች፣ የምትሰበስበው ገቢ እና ውስብስብ ሥርዓቶችን የመምራት አቅሟ የነገዋን ዕጣ ፈንታ የሚወስን ነው።

አክለውም መንግሥት በሁለንተናዊ ብልፅግና፣ በምርታማነት ማደግ፣ በኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና በሀገራዊ አንድነት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል።

በኢነርጂው ዘርፍ ኢትዮጵያ የሕዝቧን ውሳኔ ሰጪነት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እውን እንዳደረገችው ሁሉ አሁን ያገኘችው የኤሌክትሪክ ኃይል ለኬንያ፣ ለሱዳን፣ ለጅቡቲ እና ለታንዛኒያ በመትረፍ ላይ እንደሚገኝ እና ይህ የድንበር ተሻጋሪ የኃይል ትስስር የትብብር ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።

በሌላ በኩል ሀገራችን በማዕድን ዘርፍ በወርቅ ብቻ ባለፈው የበጀት ዓመት 5.6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘቷን ጠቁመው፣ የወርቅ ማዕድኗን በአዲስ አበባ በሚገኘው የከበሩ ማዕድናት ማጣሪያ በሀገር ውስጥ በማጣራት እና የምስክር ወረቀት በመስጠት ለቀጣናው ጭምር አገልግሎት መስጠት መጀመሯን አብራርተዋል።

ከዚህም ባለፈ በ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂ አማካኝነት የፋይዳ (የዲጂታል መታወቂያ) ሥርዓትን ከክፍያ እና ከዳታ ልውውጥ ጋር በማያያዝ የሕዝብ አገልግሎቶችን በቀላሉ ማግኘት የሚያስችል አሠራር መዘረጋቱን ተናግረዋል።

አፍሪካን በቴክኖሎጂው ዘርፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ እና የቀጣዩን ትውልድ አቅም ለመገንባት "የብልፅግና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ" እንደሚቋቋም የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ተቋሙ ከአፍሪካ ሀገራት የሚመጡ ተማሪዎችን በመቀበል አህጉራዊ ችግሮችን በቴክኖሎጂ የሚፈቱ ብቁ አዕምሮዎችን ለማፍራት የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ አጽንኦት ሰጥተዋል።

#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

 

በብሌን ደምበሎ

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: