የአንድ ሀገር ሕልውና የሚረጋገጠው እና የሚጸናው፣ ሉዓላዊነቱም ከዘመን ወደ ዘመን የሚያሻግረው በማይታጠፍ ተቋማዊ ክንድ ነው።
ኢትዮጵያም ለሺህ ዘመናት የነፃነት እና የሉዓላዊነቷን ታሪክ ጠብቃ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንድትሻገር ያስቻላትን የሀገር መከላከያ ሠራዊት 119ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ዛሬ “የድል ሠራዊት” በሚል መሪ ቃል እያከበረች ትገኛለች።
ይህ ዕለት ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ የዘለቀውን የዘመናዊ ውትድርና ጉዞ ወደ ኋላ መለስ ብሎ የሚቃኝ፣ አባቶች በክብር ያቆዩትን የነፃነት ሰንደቅ ልጆች በምን ዓይነት ብቃት እና ቁርጠኝነት ተረክበው እያስቀጠሉት እንደሆነ የሚመሰከርበት የትውልዶች የቃል ኪዳን መድረክ ነው።
በኢትዮጵያ ነባራዊ እውነታ የውትድርና ሙያ መደበኛ የሥራ ውል ሳይሆን የሀገር ፍቅር ከደም ዝውውር ጋር የሚዋሃድበት እና ለሕዝብ ሰላም ሲባል ሕይወትን እስከ መስጠት የሚደርስ የመሥዋዕትነት ልኬት ሆኖ ዘልቋል።
ይህ ታሪካዊ ተቋም ዛሬ የደረሰበትን ቁመና ልዩ የሚያደርገው፣ በሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ለዘመናት ሲንከባለል የመጣውን “የቀደመውን አፍርሶ እንደ አዲስ የመጀመር” አዙሪት መስበር መቻሉ ነው።
ባለፉት ዓመታት በመደመር እሳቤ የተቃኘው ወታደራዊ ሪፎርም፣ ትናንት በተለያዩ ዘመናት ሀገር ያገለገሉ አንጋፋ ጄኔራሎችን እና የጦር መሪዎችን ከዛሬው ተረካቢ ትውልድ ጋር በአንድ ማዕድ አገናኝቷል።
ነባሩን መሠረት ሳያናጉ በላዩ ላይ እያሳደጉ የመሔድ ፍልስፍና በሠራዊቱ ውስጥ ጠንካራ የተቋማዊ ባለቤትነት ስሜትን እና የጓዳዊ መተሣሠርን ፈጥሯል። ከዚህም ባሻገር መከላከያን ከወገንተኝነት በማጽዳት፣ የሥልጣን ሽግግር በተደረገ ቁጥር የማይነቃነቅ፣ ለሕገ መንግሥቱ እና ለሕዝብ የሚገዛ ፕሮፌሽናል የሀገረ መንግሥት ምሰሶ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል።
የዘንድሮውን የድል ሠራዊት በዓል ይበልጥ ትርጉም የሚሰጠው ተቋሙ ከውጭ ጥገኝነት ተላቅቆ በራስ መቻል ስትራቴጂ ያስመዘገበው የቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ እመርታ ነው። የ130 ሚሊዮን ሕዝብ ደኅንነት የሚጠበቀው በታሪክ ብቻ ሳይሆን ዘመኑን በዋጀ ወታደራዊ ሳይንስ መሆኑን በመረዳት፣ ኢትዮጵያ የጦር መሣሪያ ሸማች ከመሆን ወደ አምራችነት ተሸጋግራለች።
በሀገራችን ኢንጂነሮች እና ተመራማሪዎች ጥረት ከሆሚቾ የጥይትና የተተኳሽ ፋብሪካዎች እስከ ስካይ ዊን ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) መገጣጠሚያ እና ማምረቻዎች ድረስ የታየው ግስጋሴ፣ የሀገርን ፍላጎት ከመሸፈን አልፎ ለውጭ ገበያ የሚበቃ አቅም ፈጥሯል።
ይህ የቴክኖሎጂ አቅም በምድር ኃይሉ በዘመናዊ ሜካናይዝድ፣ በኮማንዶ እና በአየር ወለድ ልዩ ዘመቻዎች እንዲሁም በሳይበር እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት ሲደገፍ፣ በአየር ክልል ደግሞ “ሰማዩ የእኛ ነው” በሚል መርሕ ወደ አምስተኛ ትውልድ የውጊያ ቴክኖሎጂ በሚሻገር አስተማማኝ የአየር ኃይል ታጅቧል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት እና የቀጠናውን የውኃ አካላት ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በአዲስ መልክ የተዋቀረው የባሕር ኃይል፣ የሀገራችንን የመከላከል አድማስ በየብስ፣ በአየር እና በባሕር የተሟላ አድርጎታል።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ወታደር የድል ሠራዊት የተሰኘው በታጠቀው ዘመናዊ መሣሪያ እና በውጊያ አውድማ ላይ በሚያሳየው የማያዳግም እርምጃ ብቻ አይደለም። የዓለም የጦር ታሪክ ተንታኞችን ሳይቀር የሚያስደምመው የሠራዊቱ እውነተኛ ጥንካሬ የሚመነጨው ከሞራል ልዕልናው እና ከሕዝባዊ ባሕርይው ነው።
ይህ ግዙፍ ወታደራዊ አቅም የተገነባው ጦርነትን ከሩቅ ለማስቀረት ሲሆን ትንኮሳ ሲገጥመው ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ አስተማማኝ ትምህርት ሰጥቶ ሰላምን ያጸናል። በውጊያ ሰዓት የጠላትን የጥፋት ሴራ የሚያመክነው ወታደር፣ እጃቸውን ለሚሰጡ ምርኮኞች ግን የያዘውን ስንቅ እና ውኃ በማካፈል፣ ቁስላቸውን በማከም እና በመንከባከብ የሰብዓዊነትን ጥግ ያሳያል።
ንጹሐን ዜጎች እንዳይጎዱ የራሱን ሕይወት መሥዋዕት የሚያደርገው ይህ የድል ሠራዊት፣ ከሀገር ድንበር ባሻገርም ለአፍሪካ ሀገራት ነፃነት መሠረት የጣለ እና በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ክብር ከፍ ያደረገ የሰላም ዓርማ ነው።
ከሕዝብ አብራክ ወጥቶ፣ ለሕዝብ ደኅንነት ቆሞ፣ በሕዝብ ደጀንነት የሚተማመነው ይህ ሠራዊት፣ ዛሬ 119ኛ ዓመቱን ሲያከብር ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚጠብቀው ትልቅ ሀገራዊ አደራ አለ። በጠራራ ፀሐይና በዶፍ ዝናብ፣ ከቤተሰብ ርቀው በየድንበሩና በየምሽጉ ለሚዋደቁት ጀግኖች የሚሰጠው ቀዳሚው ምስጋና ለለበሱት ዩኒፎርም እና ለሙያቸው ተገቢውን ክብር መስጠት ነው።
እያንዳንዱ ዜጋ የሠራዊቱን ሥነ ልቦና እና ሞራል የሚገነቡ ሥራዎችን በመሥራት ሕዝባዊ ደጀንነቱን ማጠናከር ይኖርበታል። ከሁሉም በላይ ግን መከላከያ ሠራዊቱ በጦር ግንባር ያሳየውን የማይበገር የድል መንፈስ፣ መላው ኢትዮጵያዊ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ በመድገም የሀገራችን ቀዳሚ ጠላት የሆነውን ድህነትን ማሸነፍ ሲችል የ119 ዓመታት የዐርበኝነት አደራ ግቡን ይመታል።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: