Search

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት 119 ዓመታት የጀግንነት እና የፅናት ጉዞ

እሑድ ጥቅምት 15, 2019 80

በዓለም የታሪክ ማኅደር ውስጥ ስማቸው በወርቃማ ቀለም ከተጻፉ ገናና እና ታሪካዊ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ ቀደምቷ ናት። ለዚህ ዘመናትን የተሻገረ ነፃነት፣ የማይናወጥ ሉዓላዊነት እና የታሪክ ግርማ መቆም ደግሞ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው በማንኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የሀገርን ጥሪ በፅናት፣ በመሥዋዕትነት እና በላቀ ጀግንነት የሚመልሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን ነው።

ዛሬ በታላቅ ሀገራዊ ኩራት እና ድምቀት የሚከበረው 119ኛው የሠራዊታችን የምሥረታ በዓል የዚህን ታላቅ ሠራዊት ዘመናትን የተሻገረ የጀግንነት ታሪክ፣ ለሀገሩ ሕይወቱን አሳልፎ ለመስጠት ያለውን የማይናወጥ ቁርጠኝነት እና በሪፎርም የደረሰበትን ከፍተኛ የዘመናዊነት ደረጃ የምንዘክርበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።

የመከላከያ ሠራዊታችን የሀገርን ክብር እና የሕዝብን ደኅንነት ለማስጠበቅ በየጫካው፣ በየሸለቆው እና በየበረሃው የሚከፍለው ተጋድሎ፣ በውርጭ እና በሐሩር ሳይበገር ሀገርን ለማዳን ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥበት የላቀ ጀግንነት እኛ ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፍ መድረክ አንገታችንን ቀና አድርገን በኩራት እንድንናገር የሚያደርግ የታሪክ ገጽታችን ነው።

አባቶቹ ያቆዩለትን የጀግንነት ውርስ እና ጽናት አጣጥሞ፣ የሀገርን ዳርቻ ለማስከበር በየግንባሩ የሚዋደቀው ሀገራችንን ሁልጊዜም በነፃነት እና በሉዓላዊነት እንድናይ አድርጎናል።

ሠራዊታችን ታሪካዊ የጀግንነት ውርሱን እንደጠበቀ፣ በዘመናዊ አደረጃጀት፣ በቴክኖሎጂ ትጥቅ እና በከፍተኛ የሥልጠና ብቃት ራሱን በማነፅ የዘመኑን ሁለንተናዊ የፀጥታ ጥያቄዎች የሚመልስ ዘመናዊ እና የተቋማት ግንባታው የበቃ ኃይል መሆን ችሏል።

ይህ ጀግና ሠራዊት ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሠራሽ ፈተናዎች በተጋረጡበት ወቅት ሁሉ ተስፋ ባለመቁረጥ፣ በከፍተኛ ሀገራዊ ሥነ-ልቦና ወደፊት በመገስገስ እና ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ ፈተናዎችን ወደ ታላቅ ድል የመቀየር ልዩ ተፈጥሯዊ እና ሙያዊ ብቃት አለው።

ፈተናዎችን የድል መነሻ፣ እንቅፋቶችን ደግሞ የታሪክ ማደሻ በማድረግ የሀገርን ህልውና በደሙ ማስከበር የመከላከያ ሠራዊታችን የማይቀየር መለያ ባህሪው ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ይህ ሠራዊት የሀገር ዋስትና፣ የዜጎች የእፎይታ እና የሙሉ ደኅንነት ስሜት ምንጭ ነው።

እናቶች በሰላም የሚያደሩበት፣ ሕፃናት ያለስጋት የነገ ተስፋቸውን የሚያልሙበት፣ ገበሬው በነፃነት የሚያርስበት እና ሀገራችን የጀመረችውን የመልማት እና የመበልጸግ ጉዞ በጽኑ መሠረት ላይ እንድትቀጥል የሚያደርገው የሠራዊታችን የሌሊት እና ቀን ድካም እንዲሁም ለሀገር ፍቅር የሚከፈለው የሕይወት ገባርነት ነው።

በቃላት ሊገለጽ የማይችል የደም እና የሕይወት መሥዋዕትነት እየከፈለ፣ የራሱን ሕይወት ለአደጋ አጋልጦ የሌሎችን ሰላም እና ሀገራዊ ሕልውና የሚያረጋግጥ የሀገራችን የማይበገር ጋሻ ነው።

እንዲህ ዓይነቱ ለሀገሩ እና ለሕዝቡ የታመነ፣ ለሀገሩ ሉዓላዊነት ሲል ሕይወቱን አሳልፎ መስጠትን እንደ ትልቅ ክብር እና ጌጥ የሚቆጥር፣ ለፍትሕ፣ ለሕግ የበላይነት እና ለሰላም የሚቆም የሀገር አለኝታ የሆነ ሠራዊት ባለቤት መሆናችን ላቅ ያለ ሀገራዊ ኩራት እና ሞገስ ነው።

በዛሬው ዕለት 119ኛውን የምሥረታ በዓሉን የምናከብረው የመከላከያ ሠራዊታችን ፅናት እና ጀግንነት የትናንት ታሪካችን ኩራት፣ የዛሬ ሰላማችን ዋስትና፣ የነገ ብሩህ ተስፋችን መተማመኛ ነው።

በሔዋን ጌታቸው 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: