በሥራ እንጂ በወንጀል ኑሮን ማሻሻል፣ ሕይወትን መቀየር አይቻልም ሲል በዝዋይ ማረሚያ ቤት ለሁለት ዓመታት የቆየው የቀድሞው የሕግ ታራሚ ሙሉጌታ አበራ ይናገራል።
በመንግሥት ይቅርታ ከዝዋይ ማረሚያ ቤት በቅርቡ ከተለቀቁ 195 የሕግ ታራሚዎች አንዱ የሆነው ሙሉጌታ፥ ባገኘው ዕድል መደሰቱን ገልፆ ባለማስተዋል በሰራው ወንጀል በማረሚያ ቤቱ በነበረው ቆይታ ብዙ ትምህርት እንዳገኘ እና እንደታረመ ለኢቢሲ ዶትስትሪም ገልጿል።
ወንጀል ኑሮን ሊያሻሽልም ሆነ ሕይወትን ሊቀይር አይችልም የሚለው የቀድሞው የሕግ ታራሚ፤ ከዚህ በኋላ ተግቶ ሠርቶ በመለወጥ የበደለውን ማህበረሰብ እንደሚክስ ተናግሯል።
በማረሚያ ቤት ቆይታው በተለያየ መንገድ ማህበራዊ ሀላፊነቱን ሲወጣ እንደነበረ የሚናገረው ሙሉጌታ፥ ከሌሎች ታራሚዎች ጋር በመተሳሰብና በመከባበር ጥሩ ጊዜ እንዳሳለፈ ጠቅሶ፤ አሁን ደግሞ በተሰጠው የይቅርታ ዕድል በአዲስ ዓመት በአዲስ ተስፋ ወደ ሥራ ለመሰማራት ያለውን ጉጉት ገልጿል።
የዝዋይ ተሃድሶ ልማት ማረሚያ ማዕከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ፍቅሬ አቢዮ በበኩላቸው፥ ታራሚዎች የይቅርታ ዕድል ሊያገኙ የሚችሉባቸው የተለያዩ መስፈርቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
በመጀመሪያ ታራሚው ከመጣበት የወንጀል ባህሪ ለመላቀቅ ዝግጁ መሆኑ እና ማረሚያ ቤቱ በሚሰጠው ምክር እና ስልጠና ራሱን ለማብቃትና ለመለወጥ ፈቃደኛ መሆኑ ክትትል በማድረግ በአግባቡ እንደሚገመገም ተናግረዋል።
ምክትል ኮማንደር ፍቅሬ በማረሚያ ቤት የቆዩ የሕግ ታራሚዎች ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ የቀድሞ ባህሪያቸውን ይዘው ሳይሆን ታርመውና ተለውጠው እንደሚወጡ በመግለፅ ማህበረሰቡም በፍቅር እንዲቀበላቸው መልዕክት አስተላልፈዋል። አንዴ ያጠፋ ሰው ሁሌ ያጠፋል ማለት አይደለም ብለዋል ዳይሬክተሩ።
በዝዋይ፣ ድሬዳዋ፣ ሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤቶች እንዲሁም በሴቶች ማረሚያ እና ማረፊያ ማዕከላት በእርምት ሂደት የነበሩ እና በሥነ ምግባራቸው መሻሻል ያሳዩ 541 የሕግ ታራሚዎች በቅርቡ በይቅርታ ተለቀው ወደየመጡበት ማህበረሰብ እንዲቀላለቀሉ መደረጉ ይታወሳል።
በሃይማኖት ከበደ