Search

በሀገር አቅም የተገነባው የሰማይ ሉዓላዊነት፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የድሮን ማምረት ታሪካዊ ሽግግር

እሑድ ጥቅምት 15, 2019 54

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በዘመናዊ የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ መድረሱን የሚያሳይ እና ሀገራችን የደረሰችበትን ከፍ ያለ ደረጃ በግልጽ የሚያመላከት አዲስ ምዕራፍ ተመዝግቧል።

ሠራዊቱ ከዚህ ቀደም ለዘመናዊ የውትድርና መሣሪያዎች ምርት ሙሉ በሙሉ በውጭ ግብዓቶች እና ድጋፎች ላይ ጥገኛ ሆኖ የቆየበትን እውነታ በመቀየር፣ ዛሬ በራሱ አቅም ድሮኖችን እስከ ማምረት የደረሰበት የብቃት ማዕቀፍ ላይ ደርሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "ስካይዊን ኤሮናቲክስ ኢንዱስትሪ" (የስካይዊን የአቪዬሽንና አየር ወለድ ቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ) በይፋ መርቀው በከፈቱበት ወቅት፣ ሀገራችን ድሮኖችን የማምረት ብቻ ሳይሆን ለውጭ ገበያ ጭምር የማቅረብ እና የመላክ አቅም ላይ መድረሷን ተናግረዋል።

ይህም የኢትዮጵያን የቴክኖሎጂ ጉዞ ከፍ ያለ ምዕራፍ ላይ እንዳደረሰው የሚያሳይ ትልቅ ማሳያ ነው።

ለረጅም ዓመታት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የቁሳቁስና የቴክኖሎጂ ፍላጎቶቹን ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ብቻ እንዲመሠረት ተገድዶ የቆየ ቢሆንም፤ ዛሬ ግን ይህ የጥገኝነት ጎዳና ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ የፈጠራ አቅም እየተተካ ይገኛል።

የሀገር ውስጥ የድሮን ምርት አቅም ማደጉ የውጭ ምንዛሬን ከማዳን ባለፈ፣ በየትኛውም አስቸኳይ የጸጥታ ሁኔታ ውስጥ ብንሆን እንኳን በውጭ አቅራቢዎች ፈቃድና ጫና ላይ ሳንወሰን የራሳችንን የመከላከያ ፍላጎት በራሳችን ቴክኖሎጂ እንድንሸፍን ያስችለናል።

ይህ ስኬት የኢትዮጵያ ወጣቶች፣ መሐንዲሶች እና ተመራማሪዎች በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላቸውን የፈጠራ አቅም በተግባር ያረጋገጡበት እና ሀገራቸው በምትፈልጋቸው ስልታዊ የኢንዱስትሪ መስኮች ግንባር ቀደም ሚና መጫወት መቻላቸውን የሚያሳይ ነው።

በሀገራችን እየተሠሩ ያሉ እንደ ኤሮ ዓባይ ያሉ የድሮን ምርት ተነሳሽነቶች ለሀገር ውስጥ ዕድገት እና ለቀጣናዊ ጸጥታ ያላቸው ፋይዳ እጅግ የላቀ ነው።

እነዚህ ተቋማት ኢትዮጵያን በምስራቅ አፍሪካ የረቀቁ የጦር እና የሰላም ማስከበር ቴክኖሎጂዎች ማዕከልነት ለማብቃት ወሳኝ መሠረት ይጥላሉ።

ኢኮኖሚያዊ እና ጂኦፖለቲካዊ ተጽዕኖ በማሳደር ድሮኖችን ከፍጆታ ባለፈ ወደ ውጭ የመላክ አቅም ላይ መድረሷ፣ የሀገራችን የኢንዱስትሪ አቅም ከፍ የሚያደርግ እና በቀጣናው ያላትን ስልታዊ ድርድር አቅም የሚያጠናክር ነው።

ሠራዊታችን በዘመናዊ የአየር ወለድ የመረጃ ስብስብ፣ የቁጥጥር እና የቅኝት አቅም ሙሉ በሙሉ በራሱ አቅም እንዲደገፍ ያደርጋል።

#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በሜሮን ንብረት

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: