የኢትዮጵያ የታጠቀ ኃይል ታሪክ ዘመናትን ያስቆጠረ እና ሕዝባችን ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚነሱ ወራሪዎችን ተባብሮ በማድቀቅ ሀገራዊ አንድነቱን አስክብሮ አሁን ላደረሰው ታላቅ የምሽግ አቅም መሠረት መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪ እና የተኩስ አመራር ኃላፊ ጄኔራል ዓለምእሸት ደግፌ ገለጹ።
“የድል ሠራዊት” በሚል መሪ ቃል በተከበረው 119ኛው የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ቀን መርሐ ግብር ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ጄኔራል ዓለምእሸት፣ የዕለቱ በዓል 119ኛው የሠራዊት ቀን ተብሎ መከበሩ ዘመናዊ የሠራዊት ግንባታ መሠረት የተጣለበትን ታሪካዊ ዕለት ለማሰብ እንጂ የቁጥር ልኩ ከኢትዮጵያ ጥንታዊ ሀገረ መንግሥት ታሪክ ጋር ይመጥናል ተብሎ እንዳልሆነ ሊሰመርበት እንደሚገባ አብራርተዋል።
ጄኔራሉ አያይዘውም የሀገራችን ዘመናዊ ሠራዊት በታሪክ አጋጣሚ በርካታ ፈተናዎችን እንዳለፈ ጠቁመው፣ ኢትዮጵያን ለማቆየት እና ሕልውናዋን ለማስከበር ከፍተኛ መሥዋዕትነት የከፈለ አበራች ኃይል ሆኖ እያለ፣ በተለያዩ ዘመናት በአንድ በኩል በውጭ ወራሪዎች በሌላ በኩል ደግሞ በውስጥ ፅንፈኛ ኃይሎች የመበተን እና የመፍረስ አደጋዎችን አስተናግዶ ማለፉን አውስተዋል።
ይህንን ታሪካዊ ስብራት እና የመበተን ስጋት ለመግታት የመደመር መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ ሠራዊቱን ለማፅናት እና ተቋማዊ ክብሩን ለማስጠበቅ የተለያዩ ወሳኝ እርምጃዎች መውሰዱን ገልጸዋል።
የቀደሙት ትውልዶች ሠራዊትም ሆነ የወቅቱ ጦር ኃይል ኢትዮጵያን የመከላከል እና የመጠበቅ ሀገራዊ ጥሪን ተቀብለው እየከፈሉ ያሉት መሥዋዕትነት በሙሉ በእኩል ሚዛን እንዲታይ እና አክብሮት እንዲሰጠው ተወስኗል።
ላለፉት 119 ዓመታት አኩሪ ሀገራዊ ገድል ሲፈጽም የቆየው መለዮ ለባሽ በቅብብሎሽ ያስረከበንን ታሪካዊ ኃላፊነት ለማሰብ እና ለማስቀጠል ሲባል፣ የሠራዊቱ ቀን የሁሉንም ዘመናት መለዮ ለባሽ የሚያቅፍ የጋራ ቀን እንዲሆን ተደርጎ በየዓመቱ በጥንካሬ እንዲከበር ተደርጓል ብለዋል።
የዘንድሮው በዓል “የድል ሠራዊት” በሚል መሪ ቃል በግንባር፣ በደጀን፣ በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል የተፈጠረውን የጠና ቅንጅት እና የሠራዊቱን አኩሪ አቅም በሚያበስር አውድ ላይ ይገኛል።
ጄኔራል ዓለም እሸት ደግፌ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን እንኳን ለዚህ ደማቅ እና ታሪካዊ የሠራዊታችን በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: