የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት 119ኛ ዓመት በዓል “የድል ሠራዊት” በሚል መሪ ቃል በድምቀት በመከበር ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የመከላከያ ሚኒስትር አቶ መሐመድ እድሪስ ለሠራዊቱ አባላት የክብር እና የዕውቅና መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሚኒስትሩ በበዓሉ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር ሠራዊቱ በሀገር ውስጥም ሆነ በዳር ድንበር በጽናት በመጠበቅ፣ ዘላቂ ሰላምን በማስፈን እና የሕዝብን ሁለንተናዊ ደህንነት በማረጋገጥ ረገድ የከፈለው እስከ ሕይወት የሚደርስ መስዋዕትነት ከፍተኛ ሀገራዊ አክብሮት የሚቸረው መሆኑን ገልጸዋል።
የዘንድሮው መሪ ቃል የሠራዊቱን እውነተኛ ገጽታ የሚያሳይ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ የድል ሠራዊት ማለት በጦር ግንባር ጠላትን መክቶ ከመመለስ ባሻገር ሀገሩንና ሕዝቡን ለሁለንተናዊ ድል፣ ለዘላቂ ሰላምና ለብርሃን እድገት የሚያበቃ ጠንካራ ተቋማዊ አቅምና ራዕይ ያለው ኃይል መሆኑን አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ሠራዊቱ ከውስጥና ከውጭ የተሸረቡ አጥፊ ሴራዎችንና የሽብር እቅዶችን በበሰለ ስትራቴጂያዊ አመራር፣ በላቀ ወታደራዊ ዲሲፕሊን፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በውጊያ ብቃት መክቶ በማክሸፍ የኢትዮጵያን አንድነት በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቁን አክለዋል።
የመከላከያ ተቋሙ ተልዕኮ የሀገር ዳር ድንበርን ከመጠበቅ አልፎ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም፣ የኢኮኖሚ እድገትና ታሪካዊ የህዳሴ ጉዞ መደገፍ መሆኑን የጠቀሱት አቶ መሐመድ እድሪስ፣ በተካሄደው ጥልቅና ጠቅላላ ሪፎርም ተቋሙ በምድር፣ በአየር እና በሳይበር ምህዳሮች ያለው ሁለንተናዊ የውጊያና የደህንነት አቅም በአስተማማኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።
ዛሬ ላይ ሠራዊቱ በዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና በቴክኖሎጂ ምጥቀት ራሱን ሙሉ በሙሉ ማደሱ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህ አቅም የራሳችንን ሉዓላዊነት ከመጠበቅ ባለፈ የመላው አፍሪካ ቀንድና የክፍለ ሀጉሩን ሰላም ለማስጠበቅ የሚያስችል ስትራቴጂያዊ ዝግጁነት የፈጠረ መሆኑ ተመላክቷል።
በመጨረሻም መላው የሀገራችን ሕዝብ የታሪኩ፣ የማንነቱና የሰላሙ መከታ ከሆነው ከሠራዊቱ ጎን በመቆም የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም በጋራ እንዲያጸና ጥሪ አስተላልፈዋል።
#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: