የኢትዮጵያ ኮማንዶና አየር ወለድን የሚለየው ቀይ ቦኔት ለሰላም መስፈን የሚከፈለውን ትልቅ ዋጋ፣ ለሰው ልጆች ያለውን ጥልቅ ፍቅርና በዘመናት መካከል የተፈጠሩ ፈተናዎችን ከነፈታኙ ድል በመንሳት የተገነባውን የማይበገር የዓላማ ፅናት የሚወክል የመስዋዕትነትና የጀግንነት መለያ ምልክት ነው።
የሀገርን ሉዓላዊነት በፅኑ መሰረት ላይ ለማስቀጠል፣ የህዝቦችን ሰላማዊ ኑሮ በዘላቂነት ለማረጋገጥና በሚከሰቱ የፀጥታ ስጋቶች ላይ ፈጣን እና በዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስ የተገነባ የመከላከያ ኃይል መገንባት አስፈላጊ በመሆኑ በመደመር መንግሥት የሪፎርም ሥራዎች ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ውጤት ከተመዘገበባቸው ተቋማት መካከል የመከላከያ ሠራዊቱ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።
በዚህ መዋቅር ውስጥ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ለሀገር ሉዓላዊነት፣ ለህዝብ ደህንነትና ለቀጣናዊ መረጋጋት የተሰጠውን አደራ በብቃት ለመወጣት የተዘጋጀ ልዩ ክንፍ ሲሆን፤ የአስተሳሰቡ ቀናነትና የስብዕናው ልዕልና የላቀ በመሆኑ የትምና መቼም በሚሰጡት ልዩ ኦፕሬሽኖች በሁሉም መስክ ለቆመለት ዓላማ ያለው ፅናት በተግባር ይረጋገጣል።
ልዩ ኦፕሬሽኖችን ወስዶ ተልዕኮውን በሚወጣበት ጊዜ እልህ አስጨራሽ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትም፣ ጠላት በከንቱ ምኞቱ የሚፈጥረው መሰናክል ወይም የሚያሰራጨው የሀሰት ትርክት ሠራዊታችን ስለ ህዝብና ስለ ሀገሩ ያለውን ቀና አመለካከት አያዛባውም።
የአባላቱ የስልጠና ሂደት በመደበኛ የውጊያ ጥበብ እና በአካላዊ ብቃት ላይ ብቻ ሳይወሰን ውስብስብ የውጊያ ስልቶችን፣ ፈጣን ውሳኔ የመስጠት አቅምን፣ የአመራር ክህሎትን እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በጥልቀት ያካተተ ነው።
በመሆኑም በከባድ የተፈጥሮ መሬት አቀማመጦች፣ በአስቸጋሪ የአየር ጠባዮች እና ከፍተኛ የአዕምሮ ውጥረት በሚፈጥሩ ድንገተኛ ሁኔታዎች ውስጥ ሳይበገሩ ውጤታማ እርምጃ መውሰድ የሚያስችላቸውን ጥንካሬ አግኝተዋል።
በተጨማሪም ዕዙ በዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች፣ በላቁ የክትትል ድሮኖች እና በመገናኛ ሥርዓቶች የተደገፈ በመሆኑ በውጊያ ሜዳ የመረጃ የበላይነትንና የውሳኔ ፍጥነትን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ችሏል።
የዕዙን ወታደራዊ ዝግጁነት በየብስ፣ በተራራ እና በወንዞች ላይ ከሚሰጡ ስልጠናዎች ባለፈ ወደ ባሕር ኦፕሬሽኖችም በማስፋት በባሕር ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ የሽብር ስጋቶችን ለመከላከል እና የህዝቦችን ደህንነት ለመጠበቅ የሚያስችል አቅም እንዲኖረው ተደርጓል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም ስለ ዕዙ ሲናገሩ ኢትዮጵያ ከሶማሌ ጫፍ እስከ ምፅዋ ጫፍ በባሕር የሚያጋጥሙ የሽብር ስጋቶችን ለመመከት፣ ወንድማማች ህዝቦችን ለመደገፍና በቀጣናው ልማትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ በቂ አቅም ያለው ኤሊት ፎርስ መገንባቱን ገልጸዋል።
በመሆኑም ዛሬ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ በየብስ፣ በአየር እና በባሕር የሚሰጡ ግዳጆችን በብቃት ለመፈፀም የሚያስችል የተሟላ ወታደራዊ አቅም የገነባ ኃይል ሆኗል።
በአውደውጊያ ውሎው ጀግና እና ጀግንነት በተገናኙበትና መሳሪያና ተኳሽ በተዋሃዱበት ሁኔታ ውስጥ ጠላቱን ሲያደባይ ምድር በእሳት ብትታጠርም ጀግናው የኢትዮጵያ ኮማንዶ ሁሉንም በፅናት ጥሶ በማለፍ ታሪክ ይሰራል።
በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ እያለፈ ሀገራዊ ተልዕኮን ሲፈፅምና ህዝብን በቅንነት ሲያገለግል ዕይታው በአድማስ አይጋረድም፤ የቆመለት ዓላማ ላይ ብቻ ያተኩራል።
ባለቀዩ መለዮ ያለፈባቸውን ሁኔታዎች በማስታወስ በተቀዳጀው ድል ሳይታበይ፣ ድክመትና ጥንካሬውን በመለየት እና በየጊዜው በመሰልጠን፣ የወቅቱን ነባራዊ ሁኔታ ተመልክቶ መጭውን በመተንበይና ከሁኔታዎች አስቀድሞ ራሱን በማዘጋጀት የወኔው ግለት ሳይበርድ ለዘመናት በድል አድራጊነት እንዲዘልቅ አስችሎታል።
በአጠቃላይ በስልጠና የበቃ፣ ልዕለ ስብእና ያለው፣ ለገባው ቃል የታመነና ጀግንነትን ከቀደምቶቹ የወረሰ በመሆኑ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ በዘመናዊ ትጥቅ፣ በላቀ ስልጠና እና በጠንካራ የሀገር ፍቅር መንፈስ የኢትዮጵያን ሰላም፣ ልማትና የወደፊት ተስፋ የማስጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነቱን በላቀ ብቃት እየተወጣ ይገኛል።
#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: