የቀጨኔ–አምባሳደር–ጊዮን-ኢሬቻ–ባምቢስ የወንዝ ዳርቻ ያለው የ10 ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በይፋ ተመርቋል።
በምረቃው ላይ የተገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አህመድ ሽዴ አዲስ አበባ እያሳየች ያለው ፈጣን ለውጥ ለሌሎች ከተሞች አርዓያ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።
አፈ ጉባኤው በጉብኝታቸው ወቅት እንደተናገሩት በወንዝ ዳርቻና በኮሪደር ልማቱ የተከናወኑ ሥራዎች ከፍተኛ ጥራት ያላቸው እና አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ወደ ተሟላ የልማት ማዕከል የቀየሩ ናቸው።
አካባቢውን ንጹሕና አረንጓዴ ካደረጉት ባለፈ የንግድ ተቋማት፣ የሕፃናትና ወጣቶች መጫወቻዎች፣ የስፖርት መዘውተሪያዎች እና የመዝናኛ ስፍራዎች በስፋት ተገንብተዋል።
እንዲሁም የወንዙን ንጽሕና ለመጠበቅና የውሃ ፍሰቱን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ግንባታዎች መከናወናቸውን ደረጃቸውን የጠበቁ የእግረኛና የመኪና መንገዶች መሰራታቸውን አብራርተዋል።
ይህ የልማት ሥራ በርካታ የመኖሪያ ቤቶችና ሞሎች እንዲገነቡ መንገድ መክፈቱን ጠቁመው የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን በማጠናከርና የነዋሪዎችን የኑሮ ጥራት በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
አቶ አህመድ ሽዴ አክለውም ይህ ስኬት የሕዝብ፣ የባለሀብቶችና የመንግሥት የተቀናጀ ጥረት ውጤት መሆኑን አንስተው ባለፉት ስምንት ዓመታት በመደመር መንግሥት ከተሞችን የዕድገትና የኑሮ ጥራት ማዕከል ለማድረግ በተሰጠው ትኩረት የከተሞች ዕድገት ፍጥነቱን እንዳስቀጠለ ገልጸዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎንም በትምህርት፣ በጤና፣ በትምህርት ቤት ምገባ እና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች ተመጣጣኝ መኖሪያ ቤት በማቅረብ ረገድ ፍትሐዊ የከተማ ልማት መረጋገጡን አብራርተዋል።
#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: