Search

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የቀጣናው አስተማማኝ ኃይል ሆኗል፦ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

እሑድ ጥቅምት 15, 2019 35

የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት የቀጣናው አስተማማኝና ጠንካራ ኃይል መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

119ኛውን የመከላከያ ሠራዊት ምሥረታ ቀን አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ፣ አንጋፋው ሠራዊት ከተገነቡት ሀገራዊ ተቋማት ቀዳሚው መሆኑን አንስተዋል።

ባለፉት 119 ዓመታት በአራት የተለያዩ የመንግሥት ሥርዓቶች ውስጥ አልፎ የውጭ ወራሪዎችን እና የሀገር ውስጥ ባንዳዎችን በመመከት ሀገር አጽንቶ ማቆየቱንም አስታውሰዋል።

አሁንም በአምስተኛው የመንግሥት ሥርዓት ውስጥ ሆኖ በሕግ የተሰጠውን የሀገር ሉዓላዊነት እና አንድነት የማስከበር ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።

"ሠራዊቱ የሀገር፣ የመንግሥት ሥርዓት እና የሀገር ሥልውና ዋና ማዕከል ነው" ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ሠራዊቱ ሕጋዊ መንግሥትን ትቶ የትኛውንም የፖለቲካ አንጃ ወይም የሸፈተ ኃይል ሊተባበር እንደማይችል እና ይህም ከተቋሙ ተፈጥሯዊ ባሕርይ ውጭ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በጫካ የሚገኙ ታጣቂ ኃይሎች መሣሪያቸውን አስቀምጠው ለሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ፣ ፖለቲካ እና ሥልጣን የሚፈልጉ አካላት በሕጋዊ እና በሰላማዊ መንገድ መወዳደር እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በአቋራጭ እና ከባዕዳን ኃይሎች ጋር በመተባበር ከጫካ ሥልጣን ለመያዝ መሞከር ከንቱ ምኞት መሆኑን ጠቁመው "በጫካ መንገድ ሞክራችሁ ሲያቅታችሁ ሠራዊቱን ለማፍረስ አትንጠራሩ፤ መከላከያን ሊያፈርሱት የከጀሉትን ያፈርሳል እንጂ በመከላከያ መቃብር ላይ የሚመሠረት የሽግግር መንግሥት የለም" ሲሉ ጠንካራ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

በመሐመድ ፊጣሞ  

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: