የመደመር መንግሥት እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከዓባይ ውኃ እና ከቀይ ባሕር የሚገኘውን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ከማስከበር ውጪ ምንም ዓይነት አማራጭ እንደሌላቸው የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አስታወቁ።
ኢታማዦር ሹሙ በ119ኛው የሠራዊት ቀን በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የዓባይ ውኃ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ፀጋ መሆኑን እና ቀይ ባሕርም ኢትዮጵያውያን እንዲገለገሉበት የተፈጠረ ባሕር መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።
ሁለቱም የውኃ አካላት ለቀጣናው ሀገራት በበቂ ሁኔታ የሚዳረሱ ቢሆኑም፣ ሀብቱን ለብቻው ለመጠቅለል የሚፈልግ የውጭ ኃይል የውስጥ ተላላኪዎችን በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ ዘመቻ መክፈቱን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት እና ሕዝቦች ጋር በወንድማማችነት እና በመልካም ጉርብትና ለመኖር ፅኑ ፍላጎት ቢኖራትም፣ የውጭ ኃይሎች የውስጥ ባንዳዎችን በማሰለፍ የቀጠናውን ሰላም እያደፈረሱ መሆኑን እና ሠራዊቱም እንደ ቀደሙት አባቶች ሁሉ እነዚህን ኃይሎች እየመከተ ይገኛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ማንሰራራት የሕልውና አደጋ ያመጣብኛል ብሎ የሚያስበው እና ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሀገራችንን ሲወጋ እና ሲያዋጋ የኖረው ታሪካዊ ጠላት፣ በአሁኑ ወቅት "የአማራ ሕልውና፣ የኦሮሞ ሕልውና እና የትግራይ ሕልውና" በሚሉ መፈክሮች ውስጥ ተደብቆ ውጊያውን መቀጠሉን ኢታማዦር ሹሙ አጋልጠዋል።
ይህ የሕልውና መዝሙር ዋናውን የውጭ ጠላት ለመደበቅ የተቀመመ መርዝ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህንን መርዝ ተሸክመው የኢትዮጵያን ሕልውና ላይ አደጋ የደቀኑት የውስጥ ባንዳዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይሁንና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በውስጥ የተደራጁ ሰባት የ"ፅምዶ" እና የትብብር ቡድኖችን እንዲሁም ከጀርባቸው የቆሙ ሦስት የውጭ ኃይሎችን በድል ማሸነፉን ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ይፋ አድርገዋል።
በዚህም ሠራዊቱ የታሪካዊ ጠላቶችን እኩይ ሴራ በማክሸፍ በቀጣናው አስተማማኝ ኃይል መሆኑን በተግባር ማረጋገጡን አስታውቀዋል።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: