Search

ያልታሰበ ሲሳይ - የምስራቅ ጀርመንን ፖለቲካን ለማርገብ የተጀመረው የቪየትናም የቡና ምርት

እሑድ ነሐሴ 18, 2017 1311

ከብራዚል ቀጥሎ የዓለም ሁለተኛዋ ቡና ላኪ ሀገር ቪየትናም ናት።

አስገራሚው ነገር ግን ቪየትናም ወደዚህ የዓለማችን ታላቅ ቡና ላኪ ወደመሆን የተሸጋገረችበት መንገድ በሚገባ ታስቦበት እና ተጠንቶ የተጀመረ ሳይሆን በድንገት የመጣ መሆኑ ነው። ጉዳዩ ከጀርመን ጋር ይያያዛል።

እ.አ.አ. በ1980ዎቹ ጀርመን ምስራቅ እና ምዕራብ ተብላ ለሁለት ተከፍላ በነበረበት ወቅት በተለይ በምስራቁ ክፍል የቀዝቃዛው ጦርነት በፈጠረው የገበያ አለመረጋጋት የቡና እጥረት አጋጠመ

በወቅቱ የቡና እጥረቱ በየእለቱ ብዙ ስኒ ቡና ለሚያስፈልጋቸው ምስራቅ ጀርመናውያን ትልቅ የፖለቲካ ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይም ነበር።

ሶሻሊስታዊው የምስራቅ ጀርመን መንግስት በቡና እጥረት ምክንያት የተነሳውን የሕዝብ ቅሬታ ለመፍታት የወቅቱ የሶሻሊዝም ርዕዮት ተከታይ ከነበረችው ቪየትናም ጋር ትልቅ የግብርና ስምምነት ተፈራረመ።

 

በዚህ ስምምነት መሰረትም የጀርመን መንግስት አስፈላጊ የሆኑ የግብርና እና የኃይል መሰረተ ልማቶችን ይዘረጋል፤ ሰራተኞችን ያሰለጥናል።

በቪየትናም በኩል ደግሞ የቡና ችግኞችን በመትከል ምርት መስጠት ሲጀምሩ ግማሹን የቡና ምርት ለ20 ዓመታት ለምስራቅ ጀርመን እንድታቀርብ ስምምነት ፈጸሙ።

በዚህ መሰረት የምስራቅ ጀርመን መንግስት በሀገር ውስጥ ያለውን የቡና እጥረት ይቀርፋል ያለውን ፕሮጀክት ዕውን ለማድረግ ተነሳ። ለቪየትናም አርሶ አደሮች የሚውል እጅግ ዘመናዊ ማሽኖችን፣ የመስኖ ዝርጋታ እንዲሁም ለሌሎች የግብርና ግብዓቶችን ማሟላት ጀመረ።

በዚህም አልበቃ የሃይድሮ ኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ ገንብተው ሰራተኞችን ካሰለጠኑ በኋላ ለቡና ተስማሚ የሆነ የአየር ሁኔታ ባላት ቪየትናም በርካታ ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሮቡስታ ቡና ችግኝ ተተከለ።

ከዚህ በኋላ ምስራቅ ጀርመኖች የመጀመሪያውን የቡና ፍሬ ለመቅመስ መጠባበቅ ጀመሩ።

በዚህ መሐከል እ.አ.አ. በኦክቶበር 3 ቀን 1990 ምስራቅ እና ምዕራብ ጀርመን በመካከላቸው የነበረውን ግንብ አፍርሰው በይፋ ተዋሃዱ።

ይህን ተከትሎም ከሶሻሊስቷ ቪየትናም ጋር ውል አድርጎ የነበረው የምስራቅ ጀርመን መንግሥት ፈረሰ።

ከቪየትናም ጋር ተደርጎ የነበረው ስምምነትም ከሶሻሊስታዊ ስርዓት መውደቅ ጋር ተከትሎ ዋጋ አጣ።

 

ቪየትናምም ሳታስበው በብዙ ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የደረሰ ቡና ባለቤት ሆነች።

ሆኖም ይህ በጀርመን የተተከለው እና ምርት መስጠት የጀመረው ቡና ሀገሪቱ ከሚያስፈልጋት በላይ በመሆኑ ኤክስፖርት ለማድረግ ገዢዎችን  መፈለግ ጀመረች።

በዚህም ምክንያት ከሁለት ሺህ ቶን በላይ ቡና ልካ የማታውቀው ቪየትናም  እ.አ.አ. 1991 በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ብዛት ያለው ቡና ወደ ልካ የውጭ ምንዛሪ አገኘች።

ሀገሪቷ በስፋት ቡና መትከል ከጀመረች 40 ዓመታት ሆኗታል። ወደ ውጭ መላክ የጀመረችው ደግሞ ካለፉት 36  ዓመታት ወዲህ ነው።

በዚህ መልኩ በድንገት የተጀመረው የቪየትናም ቡና ንግድ አድጎ ላለፉት በርካታ ዓመታት ከብራዚል ቀጥሎ ሁለተኛዋ ቡና ላኪ ሀገር እንድትሆን አስችሏታል። ታዲያ በነዘህ ጊዜያት መሐል የቡና ምርቷን ለማሳደግ ሰፋፊ ሥራዎችን ማከናወኗን መዘንጋት እነደማይገባ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ይገልጻሉ።

ቪየትናም  እ.አ.አ. በ2024 ብቻ 1.32 ሚሊዮን ቶን ቡና ወደለተያዩ ሀገራት ልካለች።

 

በዋሲሁን ተስፋዬ