Search

የመደመር መንግሥት ለሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ተግቶ ይሠራል - ርዕሰ መስተዳድር ፍቅሬ አማን

ረቡዕ ጥቅምት 18, 2019 125

የመደመር መንግሥት ከሕዝብ ለተነሱ መሠረታዊ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ተግቶ እንደሚሠራ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ዞኖች የሚኖሩ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ አጠቃላይ ህዝባዊ የምክክር መድረኮችን አካሂደዋል።

በታርጫ፣ በአመያ፣ በቦንጋ፣ በሚዛን አማን፣ በቴፒ እና በጀሙ ከተሞች በተካሄዱት በእነዚሁ የጋራ የምክክር መድረኮች ላይ የተሳተፉ ነዋሪዎች፤ የመደመር መንግሥት የጀመራቸው ሀገራዊና ክልላዊ የልማት ሥራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ አስፈላጊውን አገራዊና ህዝባዊ ትብብር እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

በምክክር መድረኮቹ ላይ የተሳተፉ የሕብረተሰብ ክፍሎች በየአካባቢው የተጀመሩ የመንገድ፣ የድልድይ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የጤና እና መሰል የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተጠናቅቀው ሕብረተሰቡን ለተጠቀሚነት እንዲያበቁ መንግሥት ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም አላስፈላጊ እንግልቶችንና ብልሹ አሰራሮችን የሚያስቀሩ የመንግሥት የሪፎርም ሥራዎች ተደራሽነታቸው ይበልጥ እንዲሰፋ፣ ለወጣቶች ዝንባሌያቸውንና ክህሎታቸውን ያማከለ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር እንዲሁም ለዘላቂ ተጠቃሚነታቸው በየደረጃው ተገቢው ድጋፍ እንዲደረግ አመላክተዋል።

በከተሞች የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት ለማቅለል በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለውን ክፍተት የመሙላት፣ የንግድ ስርዓቱን የማስዘመን እንዲሁም ህግ የማስከበር እርምጃዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የተናገሩት ተሳታፊዎቹ፤ እያደገ ለመጣው የገጠርና የከተማ የልማት ጥያቄ መንግሥት በዕቅድ የተደገፈ ምላሽ እንዲሰጥና ለዚህም ስኬት ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን እንደሚቆም አስገንዝበዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን በበኩላቸው፤ በሁሉም ዞኖች በተካሄደው ህዝባዊ ውይይት ከሕብረተሰቡ ጋር ፍጹም የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

 የመደመር መንግሥት የሕዝብን ሁለገብ ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ ተግቶ እንደሚሠራ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ለዚህ ስኬት የሕዝቡ የተደመረ አቅም፣ አንድነትና አጋርነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

አክለውም በክልሉ የሚገኙ እምቅ ተፈጥሯዊ ሀብቶችን በአግባቡ በማልማትና የገቢ አማራጮችን አሟጥጦ በመጠቀም ክልሉን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተቀናጀ ርብርብ እንደሚደረግ ጠቅሰዋል።

የተጓተቱ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን የማጠናቀቅ፣ የሥራ ዕድል አማራጮችን የማስፋት እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቶችን ይበልጥ የማስዘመን ተግባራት የትኩረት ማዕከል እንደሚሆኑም አመላክተዋል።

በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤና እና በሌሎችም የማህበራዊና ኢኮኖሚ ዘርፎች እመርታዊ ለውጥ በማስመዝገብ የክልሉን ማንሰራራት በተጨባጭ ማረጋገጥ እንደሚገባ ያሰመሩበት አቶ ፍቅሬ አማን፤ ክልላዊ ሰላምና አንድነትን በመጠበቅ ለብልጽግና ጉዞ ስኬት በየደረጃው ያለው አመራርና ሕዝብ በትስስር እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።

 

በሰለሞን ባረና

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: