Search

የመደመር መጽሐፍ ለዓለም አቀፍ ፖለቲካ እጅግ ወሳኝ ነው:- የአርቲ አፍሪካ ኃላፊ

ረቡዕ ጥቅምት 18, 2019 123

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) «የመደመር» መጽሐፍ ለኢትዮጵያና ሩሲያ ታሪካዊ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለዓለም አቀፍ ፖለቲካ እጅግ ወሳኝ እና ጠቃሚ መሆኑን የሩሲያው ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን አውታር «አርቲ አፍሪካ» ኃላፊ ስቭያቶስላቭ ሸጎሌቭ ገለጹ።

ኃላፊው እንደገለጹት፣ በዓለም ላይ በርካታ ሀገራት የየራሳቸው ፖለቲካዊና ማህበራዊ ፍልስፍና ያላቸው ሲሆን፤ ኢትዮጵያም በፕላኔታችን ላይ እንዲህ ዓይነት ጥልቅ ፍልስፍና ካላቸው ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ገልጸዋል።

የመደመር መጽሐፍ ወደ ሩሲያኛ ቋንቋ በመተርጎሙ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው የተናገሩት ስቭያቶስላቭ ሸጎሌቭ፤ መጽሐፉ የዕውቀት አድማሱን በማስፋት ወደ ሌሎች ተጨማሪ የዓለም ቋንቋዎችም ሊተርጎም እንደሚገባ ገልጸዋል።

የሩሲያ ታዳሚዎች የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጥልቅ ሀሳብና ፍልስፍና በራሳቸው ቋንቋ ማግኘት እንዳለባቸው የጠቆሙት ኃላፊው፤ መጽሐፉ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጀምሮ የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነትና የፖለቲካ ትስስር ለመረዳት ለሚፈልጉ ሁሉ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።

አክለውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ“ሜዳ አቦራ” ፕሮጀክት አንሥቶ እስከ ዛሬው የሀገር መሪነት ጉዟቸው የኢትዮጵያን እውነተኛ ታሪክና የሀሳብ ጥቀት ለዓለም ማሳየት መቻላቸውን ጠቁመዋል።

አርቲ (RT) ከኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን አጋሮቹ ጋር የረጅም ጊዜ የትብብር ታሪክ እንዳለው ያወሱት ኃላፊው፤ ተቋማቸው በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ በርካታ ዶክመንተሪዎችን መሥራቱንና ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ የአፍሪካ ሚዲያ ሽልማት ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።

«የአፍሪካ አህጉር ልብ የሆነችው ኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ አጋራችን በመሆኗ እጅግ ደስተኞች ነን» ሲሉም ተናግረዋል።

 

በመሐመድ ፊጣሞ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: