Search

የድሮን ምርምር እና ልማትን ለማጠናከር የሚያግዝ ስምምነት ተፈረመ

ሓሙስ ጥቅምት 19, 2019 31

የስካይዊን ኤሮናቲክስ ኢንዱስትሪ እና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያን የኤሮናቲክስ ቴክኖሎጂ አቅም ለማሳደግ፣ የድሮን ምርምርና ልማትን ለማጠናከር እንዲሁም የአየር ላይ ቅየሳ አገልግሎትን ለማስፋፋት ያለመ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

በሁለቱ ተቋማት መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ በድሮን ዲዛይንና ምርት እንዲሁም በሥርዓት ሙከራና ማረጋገጥ፣ በሰው ኃይል ልማትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፎች ዘላቂና የተደራጀ ትብብር ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

እንዲሁም ልምድና ዕውቀትን በመለዋወጥ እና የምርምር ውጤቶችን ወደ ተግባራዊ መፍትሔዎች በማሸጋገር የሀገር ውስጥ የቴክኖሎጂ አቅምን ለማሳደግ እድል እንደሚፈጥር ተመላክቷል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ (ዶ/ር) ስምምነቱ የሁለቱን ተቋማት አቅም፣ ዕውቀት፣ የሰው ኃይልና የቴክኖሎጂ ሀብት በማቀናጀት የምርምር ውጤቶችን ወደ ተጨባጭ ምርትና አገልግሎት ለማሸጋገርና የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

የኤሮናቲክስና የድሮን ቴክኖሎጂዎች መረጃ በመሰብሰብ በአየር ላይ ቅየሳ፣ በምርምርና በተለያዩ የልማት ተግባራት ላይ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው በማንሳት የጋራ ምርምር፣ ምርት፣ ሙከራና የሥልጠና ፕሮጀክቶችን መተግበርና የተቀናጀ አመራር መስጠት ለትብብሩ ስኬት ወሳኝ በመሆኑ በፍጥነት ወደ ትግበራ መገባት እንዳለበት አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ (ዶ/ር) የመግባቢያ ሰነዱ መፈረሙ ለሀገር በቀል የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታና ለአቪዬሽን ዘርፉ እድገት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው በመሆኑ የትብብሩን አስፈላጊነት ያጎላል ብለዋል።

በተጨማሪም የባለሙያዎችን ክህሎት በማሳደግና የቴክኖሎጂ ዕውቀትን በማስተላለፍ የሀገር ውስጥ የኤሮስፔስ ዘርፍ እድገትን ለመደገፍ ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸው፣ ትብብሩ ከተቋማዊ ግንኙነት ባለፈ እንደ ሀገር በቴክኖሎጂ ራስን ለመቻል፣ የምህንድስና እውቀትን ለማስፋፋት እና ለዘላቂ ልማት አስተዋጽኦ እንዲያበረክት አመልክተዋል።

የስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰለሞን ጓዴ (ዶ/ር) ትብብሩ በሰነድ ደረጃ ብቻ ሳይገደብ፣ በፍጥነት ወደ ተግባር በመሸጋገር ተጨባጭና ዘላቂ ውጤት እንዲያመጣ ትኩረት በመስጠት እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

የብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት የስካይዊን ኤሮናቲክስ ኢንዱስትሪን የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት አስመርቆ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ድሮኖችን እያረመተ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: