አዲስ አበባ ከተማ የ2026 የከተሞች ዘላቂ ልማት ዓለም አቀፍ ሽልማት (2026 Global Award for Sustainable Development in Cities) መጎናጸፏ በከተማዋ የታየውን ዕድገት፣ ዘላቂ ልማት እና ቀጣይነት ያለው ለውጥ የሚያረጋግጥ እና ለኢትዮጵያም ታላቅ ኩራት የሚያጎናጸፍ ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
ይህ ዓለም አቀፍ እውቅና ወደፊት በድፍረት ለመመልከት መልካም አጋጣሚ መሆኑን የጠቆመው ጽሕፈትቤቱ፣ የእያንዳንዱን ከተማ ልዩ ታሪክ፣ ቅርስ እና ማንነት በመጠበቅ ዘመናዊ፣ አካታች እና ዘላቂ ከተሞችን መገንባቱን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አሳስቧል።
የከተማ ልማት ከመሠረተ ልማት ዝርጋታ የዘለለ መሆኑን በመጠቆም፣ የከተሜነት ባህልን ማሳደግ፣ ጥራት ያላቸው የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎችን መፍጠር እና ከተሞችን ለመኖር እና ለመሥራት የተሻሉ ቦታዎች ማድረግ ማለት መሆኑን አብራርቷል።
የዚህ ስኬት ራዕይ ከአዲስ አበባ ባሻገር ሊሰፋ እንደሚገባ የጠቆመው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ከሐረር እስከ ባሕር ዳር፣ ከሐዋሳ እስከ ጅማ፣ ከአርባ ምንጭ እስከ ድሬዳዋ ድረስ ያሉት እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ከተማ የዘላቂ ከተማ ልማት ማሳያ የመሆን የላቀ አቅም እንዳላቸው አረጋግጧል።
“ዛሬ አዲስ አበባ፤ ነገ ደግሞ ለእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ከተማ አዲስ ምዕራፍ” በሚል መሪ ሐሳብ ከተሞች ከታሪካቸው ሳይነጠሉ የወደፊቱን ጊዜ የሚመጥኑ እና የዘመኑን ፍላጎት የሚያሟሉ ሆኖ እንዲገነቡ ጥሪ ቀርቧል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: