Search

አፍሪካዊያን የጋራ ብልጽግናቸውን የሚያረጋግጥ የትምህርት ሥርዓት መገንባት ይጠበቅባቸዋል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

ሰኞ ነሐሴ 19, 2017 60

አፍሪካዊያን የጋራ ብልጽግናቸውን የሚያረጋግጥ የትምህርት ሥርዓት መገንባት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።

41ኛው የአፍሪካ የትምህርት ምዘና ዓመታዊ ጉባዔ የትምህርት ምዘናን ለማሸጋገር ጥራት ያለው ትምህርትና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ነው።

ጉባዔው መጻኢ ዕድላችንን ለመወሰንና የተማረ ዜጋን ለመፍጠር መሰረት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን፥ ጥራት ያለው ትምህርት ማድረስ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የአፍሪካ የትምህርት ምዘና ማኅበር ለትብብር ለዕውቀትና ለፈጠራ ምቹ መደላደል ፈጥሯል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በጋራ ትምህርትን ወደ ከፍታ እናሻግራለን  እዚህ ላይም ጠንካራ ሥራ ይጠብቀናል ብለዋል።

ለዚህም የኢትዮጵያ መታወቂያ የሆነውን የአድዋ ድል መንፈስን ተላብሰን   ትብብርና አንድነታችንን በማጠናከር፤ በትምህርት ሴክተሩ ላይ ልንደግመው እና ተግባራዊ ልናደርገው ይገባልም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ እና በርካታ የአፍሪካ ሀገራት በርካታ የለውጥ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆኑን በመጠቆምም፤ ኢትዮጵያ ሁሉም ተማሪዎች በአግባቡ እንዲመዘኑ የሚያደርግ ሥርዓትን እየገነባች መሆኑን አንስተዋል።

ይህ ኮንፈረንስም ምርጥ ተሞክሮዎቻችን ጥናቶቻችን እና ሀሳቦቻችንን የምንጋራበት ነው ሲሉ ገልፀዋል።፡

በኮንፈረንሱ 30 ሀገራት የተውጣጡ 500 በላይ ልዑካን እየተሳተፉ ሲሆን፤ 120 በላይ የምርምር ወረቀቶች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በአሸናፊ እንዳለ