Search

የአፍሪካ መጻኢ ዕድል የተመሰረተው ሕዝባዊ አንድነትን፣ ተጠያቂነትንና አካታች አስተዳደርን ማረጋገጥ በሚቻልበት አቅም ላይ ነው፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ዓርብ ጥቅምት 27, 2019 210

 “ለዕድገት መምራት” በሚል መሪ ቃል ዛሬ መካሔድ በጀመረው 2ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ንግግር አድርገዋል፡፡

የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ይህ ታላቅ አህጉራዊ መድረክ መካሄዱና መስተናገዱ ለሁሉም ታላቅ ኩራት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

በመደመር እሳቤ እየተመሩ ሕዝባዊ አንድነትን፣ ተጠያቂነትንና አካታች አስተዳደርን ማረጋገጥ የፖለቲካ አመራር የዜጎችን ሕይወት እንዲያሻሽል የሚያስችሉ ወሳኝ መሠረቶች መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገንዝበዋል፡፡

ይህም ፓርቲዎች ከምርጫ ውድድር ባለፈ አሻግረው እንዲመለከቱ፣ በመንግሥት ለውጦች የማይቀያየሩ፣ ብሔራዊና ቅድሚያ በሚሰጣቸው የረጅም ጊዜ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት እንዲፈጥሩ እና ለሀገር ጥቅም በጋራ እንዲሠሩ የሚጠይቅ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል፣ ተተኪው ትውልድ ኃላፊነቶችን እየወሰደ የሚያድግበትን ዕድሎች እያገኘ እንዲሄድ ለማድረግ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ እጅግ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ አመራር የልህቀት አካዳሚ በኩል የምትሰጠውን ሥልጠና በአህጉሪቱ ለሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክፍት ማድረጓን እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

ለሕዝባችን የተሻለ መጻኢ ዕድል የመገንባት ኃላፊነታችን ሊቀጥል ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)  መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: