የሀገር ሉዓላዊነት እና የዜጎችን ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስጠበቅ፣ በሁሉም ማዕዘናት የዳበረና ዘመናዊ አቅም ያለው መከላከያ ሠራዊት መገንባት የሕልውና ጉዳይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “በመከላከያ ስትራቴጂ አማካኝነት በሁሉም ምሰሶዎች ሸብረክ የማይል ጠንካራ ሠራዊት እየተገነባ ነው፤ መከላከያ ቴክኖሎጂን በሚገባ የሚጠቀም ተቋም አድርገነዋል፤ ይህም በውጤቱ እየታየ ነው” በማለት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መግለጻቸው፣ የመከላከያ ተቋማዊ ግንባታ የደረሰበትን የላቀ ምዕራፍ እና ስትራቴጂያዊ አቅጣጫ በግልጽ የሚያመላክት ነው።
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ዘመናዊው የመከላከያ ግንባታ በአንድ አቅጣጫ ወይም በአንድ ወቅት ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፣ በተለያዩ ማዕዘናት የተቀናጀ እና ለማንኛውም ፈተና የማይበገር አቅም መገንባትን ማዕከል ያደረገ መሆኑን ያሳያል።
ሠራዊቱ ለችግሮች ድንገተኛ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የረጅም ጊዜ ርዕይን፣ የአደጋ ትንታኔን እና የተቀናጀ ስትራቴጂያዊ ዕቅድን መሠረት ያደረገ ተቋማዊ አሠራር በመገንባት ላይ ይገኛል።
የመደመር መንግሥትም ሙያዊ ክህሎትን፣ የዲሲፕሊን ጥንካሬን እና የሀገር ፍቅር እሴትን ያጣመረ፣ እንዲሁም ከግለሰቦች ወይም ከጊዜያዊ ሁኔታዎች ባለፈ በሥርዓት የሚመራ እና የሚዘምን ሠራዊት ለማፍራት በቁርጠኝነት እየሠራ ነው።
በዛሬው ፈጣን ለውጥ በሚታይበት የደኅንነት እና የመከላከያ አውድ ውስጥ፣ መረጃን በፍጥነት መሰብሰብ እና መተንተን፣ የግንኙነት ደኅንነትን ማረጋገጥ እና ዘመናዊ የሥልጠና እና የኦፕሬሽን ሥርዓቶችን መጠቀም የተቋማትን ተወዳዳሪነት እና ውጤታማነት ይወስናል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “መከላከያ ቴክኖሎጂን በሚገባ የሚጠቀም ተቋም አድርገነዋል” ማለታቸው፣ ቴክኖሎጂን እንደ ጊዜያዊ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን እንደ ቋሚ ተቋማዊ አሠራር እና የአቅም ማጎልበቻ አካል አድርጎ የማዋሃድ ሂደትን የሚያንፀባርቅ ነው።
ቴክኖሎጂን በአግባቡ ማዋሃድ የውሳኔ አሰጣጥ ፍጥነትን እና ትክክለኛነትን ያሳድጋል፣ የሀብት አጠቃቀም ቅልጥፍናን ያረጋግጣል እንዲሁም የዝግጁነት ደረጃን ወደ ከፍተኛ ከፍታ ያሸጋግራል።
በማንኛውም የተቋም ማሻሻያ ውስጥ እውነተኛው መለኪያ በተግባር የሚመዘገብ ተጨባጭ ውጤት ነው። የስትራቴጂ እና የቴክኖሎጂ ውህደት ሲሳካ፣ ለውጡ በተግባራዊ አፈጻጸም፣ በቅንጅት ጥንካሬ እና በተቋማዊ ዝግጁነት በግልጽ ይንጸባረቃል።
የመከላከያ ሠራዊት ግንባታ በስትራቴጂ ሲመራ እና በቴክኖሎጂ ሲደገፍ፣ የሠራዊቱ ጽናት እና የመከላከል አቅም የበለጠ የተረጋገጠ ይሆናል።
በሁሉም ምሰሶዎች የተገነባ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም ተቋም መፍጠር፣ የሀገርን ሉዓላዊነት እና ደኅንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም የወደፊት ፈተናዎችን በብቃት ለመወጣት ታሪካዊ እና መሠረታዊ ምዕራፍ ነው።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: