Search

ኪስዎ ውስጥ ያለው ፓስፖርት እና የብር ኖት የት ነበር የሚታተሙት? ሦስቱን የሉዓላዊነት ቁልፎች ወደ ቤቷ እየመለሰች ያለችው ኢትዮጵያ

እሑድ ኅዳር 20, 2019 98
በኪስዎ የያዙትን ፓስፖርት እና የሚገበያዩበትን የብር ኖት ለአፍታ ይመልከቱ፤ ከእነርሱም ጎን ከኢትዮጵያ አፈር የሚወጣውን ወርቅ ያስቡ። እነዚህ የዜግነት ማንነታችን እና የኢኮኖሚ ሕልውናችን መሠረቶች ለዘመናት አንድ የሚያመሳስላቸው ክፍተት ነበር፦ ሦስቱም የሚታተሙት ወይም የሚጣሩት ከኢትዮጵያ ውጭ፣ በውጭ ተቋማት እጅ ነበር።
ይህ የደንበኝነት ጥገኝነት ዋጋው ቀላል አልነበረም። አንድ ዜጋ የጉዞ ሰነዱን ለማግኘት የውጭ ማተሚያ እስኪልክ ወራትን ይጠብቃል፤ የዜጎች የግል መረጃ እና የዳታ ሉዓላዊነት ድንበር ተሻግሮ ለስጋት ይጋለጣል፤ በየዓመቱ የሚወጣው ወርቃችንም በጥሬው እየተላከ ከፍተኛ እሴቱ በውጭ ማጣሪያዎች እጅ ይቀር ነበር።
ዛሬ ይህንን ታሪካዊ ክፍተት ከሥሩ የሚቀይር መዋቅራዊ እርምጃ በተግባር ተጀምሯል፤ የዚህ ለውጥ ሞተር ደግሞ በጓዳ ተበታትኖ ይባክን የነበረውን የመንግሥት ሀብት ቆጥሮ ወደ ሥራ ያስገባው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ነው።
የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው የልማት ድርጅቶች በእጃቸው የሚገኙ መሬትን፣ መሣሪያዎችን እና ሌሎች ንብረቶችን በዘመናዊ የሒሳብ ሥርዓት መመዝገብ እና በተጠያቂነት ማሠራት ሲጀምሩ የተቋማቱ ዋጋ እንዲያድግ ያርጋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ማብራሪያ እንዳመለከቱት፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሀብት ከጥቂት ዓመታት በፊት ከነበረበት 2.6 ትሪሊዮን ብር ወደ 9 ትሪሊዮን ብር ከፍ ብሏል።
 
በሥሩ ያሉ የልማት ድርጅቶች ዓመታዊ ገቢም ከ788 ቢሊዮን ወደ 3.1 ትሪሊዮን ብር ተሻግሮ፣ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ ለ72 ሺህ ዜጎች አዲስ የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
ይህ የተጠራቀመ ሀገራዊ ወረት በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ ሁለት ስትራቴጂያዊ ፋብሪካዎችን ወልዷል፤ ሦስተኛውንም በመንገድ ላይ አስይዟል።
በ55 ሚሊዮን ዶላር የተገነባው ቶፓን ሴኩሪቲ ኢትዮጵያ በዓለም በጥቂት ኩባንያዎች እጅ የሚገኘውን ከፍተኛ የደኅንነት ሕትመት ቴክኖሎጂ አዲስ አበባ ምድር ላይ አምጥቶታል። በዚህም የዜጎች መረጃ ሳይወጣ ፓስፖርት በሀገር ውስጥ ይታተማል፤ የቴክኖሎጂ ሽግግር ይፈጠራል፤ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም በማተም የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል።
በጥቅምት ወር የተመረቀው እና በዚያው በቦሌ ለሚ በ50 ሚሊዮን ዶላር የተገነባው ኢትዮጵያ 51 በመቶ የበላይ ባለቤትነት የያዘችበት የመጀመሪያው ብሔራዊ የወርቅ ማጣሪያ፣ አምና 5.6 ቢሊዮን ዶላር ያስገኘውን የወርቅ ኤክስፖርት ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋግራል።
በዓመት ከ600 ቶን በላይ የሀገር ውስጥ እና የጎረቤት ሀገራት የከበሩ ማዕድናትን በማጣራት፣ በጥሬ ሽያጭ ይባክን የነበረውን እሴት በሀገር ውስጥ ያስቀራል።
ለገንዘብ ሕትመት በየዓመቱ የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪና ጥገኝነት ለማስቀረት የብር ሕትመት አቅምን በሀገር ውስጥ የማስፋፋት ዕቅድ የዚሁ ሰንሰለት ሦስተኛ ማሰሪያ ሆኗል።
ፓስፖርት ለዜጎቿ ክብርና ማንነት፣ ወርቅ ለብሔራዊ ካዝናዋ፣ የገንዘብ ሕትመት ደግሞ ለገበያዋ ነጻነት በማዋል ኢትዮጵያ ተኝቶ የነበረውን ሀብቷን ቆጥራ፣ በሰው እጅ የነበሩትን ሦስቱን የሉዓላዊነት ቁልፎች ወደ ራሷ ቤት እያስገባች ትገኛለች።
በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: