Search

የ4 ቀኑን የኢትዮጵያ ጅቡቲ ጉዞ በ17 ሰዓት

እሑድ ኅዳር 20, 2019 184

በኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የባቡር ጥገና ወርክሾፕ ውስጥ ለዓመታት የሁሉም ሰው ዐይን የሚያርፍባት አንዲት ትንሽ ተሽከርካሪ ነበረች፤ ስሟ ‘ሬይል ካር’ ይባላል።

ይህች አንድ ለእናቷ የሆነች መኪና የተበላሹ ግዙፍ ባቡሮችን እየጎተተች ወደ ጥገና ጋራዥ የምታስገባ እና የተጠገኑትን ወደ ሐዲድ የምታስወጣ ብቸኛ ማንቀሳቀሻ ነበረች። ችግሩ ግን ግልጽ እና አስፈሪ ነበር፤ ‘ሬይል ካር’ አንድ ቀን ተበላሽታ ብትቆም፣ በቢሊዮን ዶላር የተገነባው የጥገና ማዕከል አብሯት ይቆማል።

ያቺ ትንሽ መኪና ኢትዮጵያ ለአንድ መቶ ሠላሳ ዓመታት በባቡር ዘርፍ የኖረችበትን የቴክኖሎጂ ጥገኝነት ቁልጭ አድርጋ የምታሳይ ምልክት ነበረች። ሐዲዱ የሚዘረጋው በኢትዮጵያ ምድር ላይ እና በኢትዮጵያ ሕዝብ ወጪ ቢሆንም፣ ከመጀመሪያው የባቡር ታሪካችን አንሥቶ ከዐሥራ ሁለት ዓመታት በፊት እስከተገነባው ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ባቡር ድረስ ግንባታው፣ ጥገናውም ሆነ አስተዳደሩ በውጭ ኩባንያዎች እና በውጭ ዜጎች እጅ ነበር።

ዛሬ ወደ ጥገና ማዕከሉ ጎራ ያለ ሰው ግን ‘ሬይል ካር’ ብቻዋን እንዳልሆነች ይመለከታል። የአደጋውን ክብደት የተረዱት ኢትዮጵያውያን የባቡር መሐንዲሶች የውጭ አምራች እስኪመጣ እጃቸውን አጣጥፈው ከመጠበቅ ይልቅ፣ በራሳቸው እውቀት እና ዲዛይን ተጨማሪ የባቡር አካላት ማንቀሳቀሻ ተሽከርካሪ ሠሩ።

ባለሙያዎቹ በራስ አቅም የሠሯትን ፍርጎ ጎታች መኪና “መደመር 01” የሚል ስያሜ ሰጥተዋታል። እነዚህ ወጣት ባለሙያዎች በዓለም አቀፍ የባቡር ጥገና ስታንዳርድ 34 ቀናት የሚፈጅን እና ውጭ ሄዶ ካልተጠገነ አይሠራም የተባለን ከባድ ባቡር ጥገና፣ በ15 ቀናት ብቻ አጠናቅቀው ወደ መስመር ሲያስገቡ መመልከት በዘርፉ ውስጥ የተፈጠረውን የአዕምሮ እና የአቅም ነጻነት ከቃላት በላይ ይናገራል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ፣ የኢትዮጵያ የባቡር ዘርፍ ከውጭ የማኔጅመንት ኮንትራት ወጥቶ ወደ ሀገር ውስጥ የአቅም ሽግግር በተሟላ ሁኔታ እየገባ መሆኑን ሲገልጹ፣ በፓርላማ የተነገረው ፖሊሲ እና መሬት ላይ ያለው የመደመር 01 እውነታ የአንድ ታሪክ ሁለት ገጾች ሆነው ይገጣጠማሉ።

ከለውጡ በፊት የነበረው ሥርዓት የኢኮኖሚያችን የደም ሥር የሆነውን የባቡር መሠረተ ልማት በመዘርጋት ረገድ አመርቂ ሥራ መሥራቱ የማይካድ ሐቅ ነው። ይሁንና መስመሮቹ የተገነቡት ከፍተኛ ወለድ ባለው የንግድ ብድር በመሆኑ፣ ግንባታው ተጠናቅቆ ወደ ሙሉ አገልግሎት ሳይገባ የብድር መክፈያ ጊዜው ደርሶ ሀገራችንን ለከባድ የዕዳ ጫና ዳርጓታል።

አስተዳደሩም በውጭ ኮንትራት ሥር ስለነበር ምንዳ ያመጣል የተባለው ፕሮጀክት የውጭ ምንዛሪ የሚያፈስ ሸክም ሆኖ ቆየ። ዛሬ ግን በተከናወነው የአስተዳደር እና የተቋም ሪፎርም ኦፕሬሽኑ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ተይዟል፤ ቆመው የነበሩ የተበላሹ ባቡሮች እየተጠገኑ ወደ ሥራ በመግባታቸውም የመንገደኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ከአምናው በከፍተኛ ደረጃ አድጓል።

የተገዛን ባቡር ማሽከርከር አንድ እርምጃ ሲሆን፣ የተጎዳን ግዙፍ የሐዲድ መሠረተ ልማት ያለ ውጭ ተቋራጭ በራስ አቅም መጠገን እና አዲስ መገንባት ግን የዘርፉ እውነተኛ የሉዓላዊነት መለኪያ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ እንዳብራሩት፣ የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዛሬ ባቡር ከማስተዳደር ተሻግሮ የሐዲድ መስመሮችን በራሱ ባለሙያዎች ወደ መጠገን እና መገንባት አድጓል።

ለዚህም በሰሜን ምሥራቅ የሀገራችን የንግድ መተላለፊያ ላይ የሚገኘው የአዋሽ–ኮምቦልቻ–ወልዲያ/ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ተጨባጭ ማሳያ ነው። በመሬት መንቀጥቀጥ እና በጎርፍ አደጋ ከባድ ጉዳት ደርሶበት የነበረው ይህ መስመር፣ የውጭ ኮንትራክተር እና አዲስ ብድር ሳይጠበቅ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን በጠበቀ ጥራት በራሱ በኮርፖሬሽኑ ባለቤትነት በፍጥነት እየተገነባ ይገኛል።

እስካሁን ወደ 100 ኪሎ ሜትር የሚጠጋው የመልሶ ግንባታ ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ቀሪው ክፍል ከአንድ እስከ አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ አልቆ መስመሩ ሙሉ በሙሉ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል።

ይህ በራስ አቅም የመገንባት እና የቆዩ ስህተቶችን የማረም ጥበብ በገላን መልቲፐርፐዝ ፖርት ላይ ደግሞ ይበልጥ አስገራሚ በሆነ መንገድ ይታያል። ቀደም ሲል የማራገፊያ ሲቪል መሠረተ ልማት ሳይዘጋጅላቸው ተገዝተው የመጡ የብትን ጭነት ዋገኖች ለ12 ዓመታት ያለ አንዳች ሥራ ቆመው ቆይተው ነበር። በዚህም ምክንያት በመርከብ የሚመጣው የአፈር ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ ላይ እየተራገፈ፣ እዚያው በከረጢት እየተሞላ እና እየተሰፋ በባቡር ይጫን ስለነበር፣ የሎጂስቲክስ ሰንሰለቱን ከማርዘሙ ባለፈ ሀገራችንን በውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላት ነበር።

የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እና የሀገር ውስጥ መሐንዲሶች ቡድን ይህንን የ12 ዓመት ማነቆ ለመፍታት ውስብስብ የውጭ ቴክኖሎጂ አልጠበቁም። ቀላል የፊዚክስ ‘የስበት ሕግ’ (Gravity Theory) በመጠቀም ዘጠኝ ሜትር ወደ መሬት የገባ እና ስምንት ሜትር ወደ ላይ የወጣ፣ በድምሩ ከ17 ሜትር በላይ ከፍታ ያለው ዘመናዊ የብትን ማዳበሪያ ማራገፊያ መጋዘን በአራት እና አምስት ወራት ውስጥ ገንብተው አጠናቀቁ። ዛሬ ማዳበሪያ ጅቡቲ ላይ ሳይታሸግ በቀጥታ በብትን ዋገኖች ተጭኖ ገላን ላይ ይራገፋል፤ የውጭ ምንዛሪ ብክነቱ ቀርቶ ምርቱ ለአርሶ አደሩ በፍጥነት እና በተመጣጣኝ ዋጋ መድረስ ጀምሯል።

ከስድስት እና ስምንት ወራት በፊት 2 ሔክታር ብቻ የነበረው የቀድሞው የእንዶዴ ፍራይት ያርድ፣ ዛሬ በ40 ሔክታር ላይ ወደ ተዘረጋ አረንጓዴ እና ለአካባቢ ተስማሚ ገላን መልቲፐርፐዝ ፖርት ተቀይሯል። በውስጡ 17 ኪሎ ሜትር አዲስ የባቡር መስመር በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ተገንብቶ በአንድ ጊዜ አራት ባቡሮችን መቀበል እና መሸኘት የሚያስችሉ አራት መስመሮች እና ስድስት ያርዶች ተፈጥረዋል። በዚህም የኮንቴይነር ማስተናገድ አቅሙ በ16 እጥፍ፣ የማዳበሪያ አያያዝ በ6 እጥፍ፣ የባቡር ማጓጓዝ አቅሙ ደግሞ በ4 እጥፍ ማደግ ችሏል።

በወደቡ ውስጥ የሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ የጉምሩክ ኮሚሽን፣ የማሪታይም ባለሥልጣን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአንድ መስኮት ተቀናጅተው የገቢ እና የወጪ ንግድ ኮንቴይነሮችን በተለያየ አቅጣጫ የሚያስተናግዱበት ሙሉ የጉምሩክ ቦንድድ ወደብ መሥርተዋል። ባቡር በሐዲድ ላይ ብቻ የሚወሰን በመሆኑም፣ ድርጅቱ በራሱ ባለቤትነት ባስመጣቸው ዘመናዊ የቮልቮ ከባድ የጭነት መኪኖች ጭነቱን ከሐዲድ ተረክቦ እስከ ደንበኛው እና እስከ ገበያው በር ድረስ ያደርሳል።

በዚህ የተቀናጀ ሰንሰለት ከጅቡቲ እስከ መሐል ሀገር በሌሎች ትራንስፖርቶች ከሦስት እስከ አራት ቀናት ይፈጅ የነበረው ጉዞ ከ17 ሰዓት በታች ወርዷል፤ ሀገራችንም ከጠቅላላ የትራንስፖርት ወጪዋ ከ35 እስከ 40 በመቶ መቆጠብ ችላለች።

ከዚህ ሁሉ ጀርባ ግን አንድ ወሳኝ የፋይናንስ ታሪክ አለ። በባቡር ሞተር እና መገጣጠሚያው ዘርፍ የመንግሥት እና የግል አጋርነት ሞዴል ጥቅም ላይ ሲውል፣ ይህ ግዙፍ የገላን መልቲፐርፐዝ ፖርት የተገነባው ግን ያለ አንዳች የውጭ ብድር እና ያለ መንግሥት በጀት ድጎማ ነው። ትናንት ወደ ኪሳራ ያመራ የነበረው የባቡር ድርጅት ወደ ትርፋማነት ተሸጋግሮ፣ ከራሱ ገቢ መልሶ ኢንቨስት በማድረግና መቶ በመቶ የሀገር ውስጥ ባለሙያዎችን በማሰማራት የገነባው የፋይናንስ ነጻነት አብነት ሆኗል።

ትናንት ሬድ ካር ብትበላሽ ምን ይውጠናል ብሎ ይሰጋ የነበረው የኢትዮጵያ የባቡር ዘርፍ፣ ዛሬ በመደመር 01 የራሱን ፈጠራ አስጀምሮ፣ በአዋሽ–ኮምቦልቻ 100 ኪሎ ሜትር ሐዲድ በራሱ መሐንዲሶች እየጠገነ፣ በገላን ደግሞ የግል ኢንዱስትሪዎችን ከዓለም ገበያ ጋር በ17 ሰዓት እያገናኘ ይገኛል። ሐዲዱ አሁን የዕዳና የውጭ ጥገኝነት ማስታወሻ አይደለም፤ የኢትዮጵያውያን እውቀትና ኢኮኖሚ በራሱ ሞተር ወደ ፊት የሚምዘገዘግበት የሉዓላዊነት መስመር እንጂ።

በነቢዩ ወንድወሰን

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: