በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከበረው 21ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በበርካታ የታሪክ እጥፋቶች ታጅቦ እንዲከበር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
በአፈ ጉባዔዋ የተመራ ቡድን በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት እና በኦሮሚያ ክልል አስተናጋጅነት በጅማ ከተማ ለ21ኛ ጊዜ ለሚከበረው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል እየተደረገ ያለውን የመጨረሻ ምዕራፍ ዝግጅት በከተማዋ ተዘዋውሮ ተመልክቷል።
በምልከታው ወቅትም በክልሉ፣ በዞኑና በከተማው አመራሮች ከፍተኛ ቅንጅት በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አረጋግጧል።
አፈ ጉባዔ ሙፈሪሃት ካሚል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ በዓሉ በሕብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ እንዲከበርና የኢትዮጵያን የስልጣኔ ደረጃ በሚያሳይ መልኩ እንዲዘጋጅ የተከናወነው ተግባር በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው።
ቀኑ በድምቀት እንዲከበር ሁሉም ባለድርሻ አካላት እያደረጉት ያለው ርብርብ የሚበረታታ መሆኑንም መግለጻቸውን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: