Search

ለብሔራዊ ጥቅም መከበር የመገናኛ ብዙኃን ሚና

ሰኞ ነሐሴ 19, 2017 47

የመገናኛ ብዙኃን ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) 30ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን አስመልክቶ “የመገናኛ ብዙኃን ለብሔራዊ ጥቅም እና ሰላም” በሚል መሪ ሐሳብ የሚዲያ ፎረም እየተካሄደ ነው።


በመድረኩ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ አቶ አማረ ሰጤ እንዲሁም የክልሉ ክፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የአሚኮ አመራር እና ሠራተኞች ተገኝተዋል።


የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአሚኮ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉቀን ሰጥዬ፣ አሚኮ ላለፉት 30 ዓመታት ለኅብረተሰብ ለውጥ እየሠራ የሚገኝ እና ከጊዜ ጊዜ ራሱን በሰው ኃይል፣ በመሣሪያ እና በዘመናዊ አሠራር እየለወጠ በአሁን ወቅት በ12 ቋንቋዎች ለሕዝብ እየደረሰ የሚገኝ ሚዲያ ነው ብለዋል።

አሚኮ ባለፉት ዓመታት ክልሉ ባጋጠመው የፀጥታ ችግር ተፈትኖ ለሕዝብ እና መንግሥት ወገንተኛነቱን በተግባር ያስመሰከረ ስለመሆኑ የገለጹት ደግሞ የክልሉ ምክርቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ አማረ ሰጤ ናቸው።

በመድረኩ ብሔራዊ ጥቅም እና የሚዲያ ድርሻ እንዲሁም በግጭት ወቅት የሚዲያ ሚና የተመለከቱ ሁለት የመወያያ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጓል።

ብሔራዊ ጥቅም እና የሚዲያ ሚና ላይ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፣ ብሔራዊ ጥቅም የሀገር እና ትውልድ ኅልውና እንጅ የፖለቲካ አጀንዳ አይደለም ሲሉ አስረድተዋል።

ለብሔራዊ ጥቅም መረጋገጥ የሚዲያዎች ሚና እና ኃላፊነት ዕድሎች እና ተግዳሮቶች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በራሔል ፍሬው

#EBC #ebcdotstream #AMECO #media #nationalinterest #peace