የአንድ ሀገር የውጭ ፖሊሲ፣ የኢኮኖሚ ጥንካሬ እና የሕዝቦቿ መፃኢ ዕድል የሚወሰነው በይዞታዋ ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮ በታደለችው ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ጭምር ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ዓባይ እና ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ሕልውና መሠረቶች ናቸው፤ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይዞ በጂኦግራፊያዊ እስር ቤት ውስጥ መቀጠል ለቀጣናውም ሆነ ለሀገራችን ዘላቂ አይሆንም” በማለት ያስተላለፉት መልዕክት፣ በቀጣናው አቀፋዊ እውነታዎች ላይ የተመሠረተ የታሪክ እና የጂኦ-ፖለቲካ ጥሪ ነው።
ይህ አቋም የቀጣናውን ልማት፣ የደኅንነት ትሥሥር እና የኢትዮጵያን የወደፊት የኢኮኖሚ ጉዞ መሠረት ያደረገ ስትራቴጂያዊ እይታን ያንጸባርቃል።
ዓባይ ለኢትዮጵያውያን የብሔራዊ ማንነት እና የዕድገት ተስፋ ነው። ኢትዮጵያ የዓባይ ውኃ ከ80 በመቶ በላይ የምታመነጭ ሀገር በመሆኗ፣ ይህን ተፈጥሯዊ ጸጋ ለሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት እና ለግብርና ልማት መጠቀም የሕልውና ጉዳይ ነው።
የኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት ውጤት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ ሀገራችን ተፈጥሯዊ ሀብቷን በመጠቀም ከድህነት ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት በተግባር ያሳየ ነው።
የዓባይ ሀብት በፍትሃዊነትና በምክንያታዊነት ጥቅም ላይ ሲውል፣ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የታችኞቹን የውኃ ተጠቃሚ ሀገራት ኤሌክትሪክ በማቅረብ የምስራቅ አፍሪካን የኢኮኖሚ ትሥሥርን ያጠናክራል።
ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ሀገር ቀጥተኛ የባሕር በር ሳይኖራት መቅረቷ የኢኮኖሚ ዕድገቷን የሚገታ ትልቅ ፈተና ነው። የዓለም አቀፍ ልምዶች እንደሚያሳዩት፣ ትላልቅ የሕዝብ ቁጥር እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ያላቸው ሀገራት የባሕር በር አለመኖራቸው ለትራንስፖርት እና ንግድ ወጪ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል።
የባሕር በር አለመኖር በየዓመቱ ለወደብ ኪራይና ተያያዥ አገልግሎቶች የምትከፍለውን ቢሊዮን ዶላሮች ወጪ ያንራል። ይህም የሀገር ውስጥ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ያደርጋል።
የቀይ ባሕር ቀጣና ሰላምና መረጋጋት ያለ ኢትዮጵያ ንቁ ተሳትፎ እና ድርሻ አስተማማኝ ሊሆን አይችልም። የሀገራችን የሕዝብ ብዛትና ስትራቴጂያዊ ቦታ በቀጣናው ጸጥታ ላይ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው።
በጂኦግራፊያዊ እስር ቤት ውስጥ መቆየት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ዘላቂ ሰላም አይጠቅምም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳመለከቱት፣ መፍትሔው በጠብ አጫሪነት ሳይሆን በጋራ የመልማት መርህ ላይ የተመሠረተ ድርድር እና የባሕር በር አማራጮችን በሰላማዊ መንገድ ማግኘት ነው።
ዓባይ እና ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ያለፈው ታሪክ፣ የወቅቱ ውጥረት እና የወደፊቱ ተስፋ መገናኛዎች ናቸው። የሕዝቦች የኢኮኖሚ እና የደኅንነት ፍላጎት በበጎ ፈቃድና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ሲመለስ፣ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአጠቃላይ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ዘላቂ ብልጽግና እና መረጋጋት መንገድ ይከፍታል።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: