የኢኮኖሚያዊ ጥንካሬ የሚለካው በእድገት መጠኑ ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ እና የጂኦፖለቲካ ውጥረቶች መካከል ምርትና አገልግሎትን ሳያቋርጡ የመቀጠል አቅም ጭምር ነው።
በቅርብ ዓመታት በቀይ ባሕር እና በስዊዝ ካናል አካባቢ የተፈጠሩ የጂኦፖለቲካ ውጥረቶች በዓለም ንግድና የትራንስፖርት ሰንሰለት ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥረዋል። ይህም የሀገራትን ኢኮኖሚ ለውጫዊ ተጽዕኖዎች ይበልጥ ተጋላጭ አድርጎታል።
በዚህ ዓለም አቀፍ ወጀብ መካከል ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የጀመረችው ሪፎርም፣ የምርት፣ የተቋማት፣ የሎጂስቲክስና የፋይናንስ ሥርዓቷን በማጠናከር የኢኮኖሚ ጽናቷን እንድታሳድግ አስችሏታል።
የዚህ ለውጥ አንዱ ማሳያ የኢትዮ - ጅቡቲ ባቡር ኮርፖሬሽን ያስመዘገበው ውጤት ነው። ኮርፖሬሽኑ ካለፉት ዓመታት የአሠራር ደረጃ ተሻግሮ የትርፋማነት፣ የጭነትና የመንገደኞች ማጓጓዝ አቅሙን ማሳደጉ ለወጪ ንግድ መሳለጥ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ነው።
በተለይም ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው የቡና ወጪ ንግድ በባቡር መጓጓዙ፣ ምርቶችን በፍጥነትና በተሻለ ወጪ ወደ ዓለም ገበያ ለማድረስ ትልቅ አቅም ፈጥሯል።
በተመሳሳይ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ድርሻ ከግብርናው መብለጡ ኢኮኖሚው ወደ መዋቅራዊ ሽግግር እየገባ መሆኑን ያሳያል። የማምረቻ አቅምን ማሳደግ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ማስፋፋትና የሀገር ውስጥ ጥሬ ዕቃዎችን በሀገር ውስጥ ማቀነባበር የተጨማሪ እሴት ፈጠራንና የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን ይበልጥ ያሳድጋሉ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሀገራዊ ሀብትን በብቃት በማስተዳደር የተቋማዊ ለውጡ ሌላኛው ማሳያ ሆኗል። የተቋሙ ሀብትና ገቢ ማደግ፣ የግብር አስተዋጽኦ መጨመርና በሥሩ ባሉ ድርጅቶች የተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች፣ ሀገራዊ ሀብትን በተሻለ አቅም ወደ ልማት የማዋል አቅጣጫን ያመለክታሉ።
የባንኮች ተቀማጭ ሀብት ማደግ፣ የሞባይል ፋይናንስ ተጠቃሚዎች መብዛትና የዲጂታል አካውንቶች መስፋፋት የገንዘብ ዝውውር ሥርዓቱን እያዘመኑት ነው። ከዚህም ባለፈ የውጭ ምንዛሪ ክምችት መጨመር፣ የወጪ ንግድ ሚዛን መሻሻልና የብድር ግዴታዎችን የመወጣት አቅም መጠናከር ሀገራችን ውጫዊ ጫናዎችን የመቋቋም አቅሟን ያሳያሉ።
በመሆኑም ኢትዮጵያ በምርት፣ በተቋማዊ አቅም፣ በሎጂስቲክስና በፋይናንስ ዘርፎች እያከናወነች ያለው ለውጥ ኢኮኖሚዋን ከውጫዊ ተጽዕኖዎች የመቋቋም አቅም ወዳለው መዋቅር እያሸጋገረው ይገኛል። የኢኮኖሚ ጽናት የሚገነባውም በአንድ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን፣ የተለያዩ ሀገራዊ አቅሞችን በማስተሳሰር ነው።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: