Search

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ታሪካዊ ስኬት እስከ ኮፕ32

ሰኞ ጥቅምት 30, 2019 90

ለረጅም ዓመታት የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ምሰሶ፣ የሰላም ድልድይ እና የአንድነት ምልክት ሆና የዘለቀችው ኢትዮጵያ፣ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ዘርፍ ከተሳታፊነት ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ አዘጋጅነት የተሸጋገረችበትን ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ስኬት አስመዝግባለች።

የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫና የአህጉሪቱ የዲፕሎማሲ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ በርካታ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉባኤዎችን በማስተናገድ የምትታወቅ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) በይፋ እንድታስተናግድ መመረጧ የአህጉራዊ የመሪነት ሚናዋ ማረጋገጫ ሆኗል።

ለዚህ ታሪካዊ ድል እና ክብር ዋናው መሠረት ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ጥበቃ ዘርፍ ያስመዘገበቻቸው ተጨባጭ ስኬቶች በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ እውቅና ማግኘታቸው ነው።

በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የ"አረንጓዴ ዐሻራ" ኢኒሼቲቭ ሚሊዮኖችን በማንቀሳቀስ የተራቆተ መሬት ወደ ነባር ተፈጥሯዊ ይዞታው በመመለስ እና የታዳሽ ኃይል አማራጮችን በማስፋት ረገድ የተከናወኑ ተግባራት ለውጤቱ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ከችግር ተናጋሪነት ወደ መፍትሔ አመንጪነት ያደረገችው ይህ ሽግግር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተአማኒነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት አሳድጎታል።

እ.ኤ.አ. ሕዳር 2025 በብራዚል ቤሌም ከተማ በተካሄደው የኮፕ30 (COP30) ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ያቀረበችው የዕጩነት ጥያቄ ድጋፍ ያገኘ ሲሆን፣ አፍሪካውያን ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ አንድ ወጥ አቋም መያዛቸውን ተከትሎ እ.ኤ.አ. ከሕዳር 8 እስከ 19 ቀን 2027 ኮፕ32 ጉባኤን በአዲስ አበባ እንድታስተናግድ በይፋ ፀድቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ውሳኔውን አስመልከተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ኮፕ32ን እንድታዘጋጅ ይህን ትልቅ ኃላፊነት በመስጠቱ ታላቅ ክብር እንደሚሰማቸው ገልፀው፣ ጉባኤው ኢትዮጵያን ከብዙ ንግግር በላይ በተጨባጭ ሥራዎቿ ገልጣ ለዓለም የምታሳይበት ታላቅ መድረክ እንደሚሆን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ኮፕ32ን ማዘጋጀቷ በአየር ንብረት ድርድር ወቅት የአፍሪካን የጋራ አቋም በዓለም አቀፍ መድረክ ለማጠናከርና የአህጉሪቱን የመፍትሔ አቅም ለማሳየት ያስችላታል።

በተጨማሪም ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ሥራዎች የሚሆን ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ለማቅረብና አጋርነትን ለማጠናከር መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የጉባኤው ተሳታፊዎች የሀገራችንን የቱሪዝም መስህቦች በሚጎበኙበት ወቅት ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ ኢኮኖሚውን በከፍተኛ ደረጃ ይደግፋል።

በአጠቃላይ ይህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ለኢትዮጵያ ከክብር ባሻገር ለሰው ልጅ መኖሪያ ምድር ጥበቃ ያላትን ቁርጠኝነት፣ የማይበገር ዲፕሎማሲና የተፈጥሮ ጠባቂነት መሪነቷን በተግባር የምታረጋግጥበት ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።

 

በብሌን ደምበሎ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: