Search

በ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወጭ በአማራ ክልል የማዕድን ላብራቶሪ ሊገነባ ነው

ሰኞ ጥቅምት 30, 2019 101

ለጌጣጌጥ፣ ለኮንስትራክሽን፣ ለኢንዱስትሪ እና ለኃይል ማመንጫ የሚሆኑ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የሀብት ማዕድናት የዕድል መድረክ የሆነው አማራ ክልል፤ ግራናይት፣ ሲርካ፣ ኦፓል፣ ወርቅ፣ ሳፋየር፣ ኢምራልድን ጨምሮ የበርካታ ሃብት ባለቤት ነው።

ይሁን እንጂ ይህንን ታላቅ ሀብት በማጥናት፣ በመለየትና በብቃት በማከማቸት ተጠቃሚ ለመሆን ሰፊ የቤት ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ የሚታወቅ ሲሆን የአማራ ክልል ማዕድን ቢሮ እነዚህን ክፍተቶች በመሙላት ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ታሪካዊ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።

የአማራ ክልል ማዕድን ቢሮ ኃላፊ ኀይሌ አበበ እንደገለጹት ቢሮው በ2018 በጀት ዓመት ብቻ በማዕድን ሀብት 131 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የሚገመት የውጭ ምርትን በሀገር ውስጥ መተካት ችሏል።

በዚያው ዓመት ክልሉ 357 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ያቀረበ ሲሆን አሁን ደግሞ በ2019 በጀት ዓመት 2 ሺህ ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለማቅረብ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ይገኛል።

አሁን ባለው የሩብ ዓመት አፈጻጸምም 431 ኪሎ ግራም ወርቅ መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን አማራ ክልልን በወርቅ ምርት ቀዳሚ የማድረግ ግብ ተይዞ እየተሠራ ነው።

ከዚህም ባሻገር እንደ ወርቅ፣ ሊትየም፣ ኮፐር እና ብረት ያሉ ስትራቴጂክ ማዕድናት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በመሠራቱ ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ይጠበቃል።

ዘርፉን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤታማ ለማድረግም የክልሉ መንግሥት በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የማዕድን ላብራቶሪ በ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ለመገንባት አቅዶ ወደ ሥራ መግባቱ ተገልጿል።

ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት እውን መሆኑ የማዕድን ጥናት ናሙናዎችን ወደ ውጭ የመላክ እንግልት ቀርቶ በሀገር ውስጥ እንዲመረመሩ የሚያስችል ታላቅ ምዕራፍ የሚከፍት ነው።

 

የአሚኮ ዘገባ እንደሚያመላክተው ይህ የልማትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ጉዞ የክልሉን ብቻ ሳይሆን የጠቅላላ የሀገራችንን የኢኮኖሚ ከፍታ የሚያረጋግጥ ነው።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: