Search

ከአዳማዋ የመጀመሪያ ችግኝ እስከ ውቅያኖስ ውስጥ ቆሞ የተሟገተው ሚኒስትር — የዓለም መሪዎችን እንቅልፍ የሚነሳው የኮፕ (COP) ጉባኤ ያልተሰሙና አስገራሚ ታሪኮች

ሰኞ ጥቅምት 30, 2019 149
ግንቦት 18 ቀን 2011 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመጀመሪያዋን የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ለመትከል ወደ መሬት ከማጎንበሳቸው በፊት "ዛሬ አምስት ሺህ ችግኝ ተዘጋጅቷል፤ ይሄን አምስት ሺህ ችግኝ በመትከል በጋራ 'ሀ' ብለን ከአራት ቢሊየኑ 5 ሺህ ዛሬ እንቀንሳለን" በማለት ታሪካዊውን ጥሪ አቀረቡ።
በዚያች ዕለት ከጉልበታቸው ዝቅ ብለው፣ እፍኝ አፈር ዘግነው የተከሏት ያቺ ለጋ ቡቃያ በሚሊዮኖች የጣት አሻራ ታጅባ ኢትዮጵያን አረንጓዴ ማልበስ ብቻ ሳይሆን ቅርንጫፎቿን ወደ ዓለም የዲፕሎማሲ ሰማይ አሳድጋ 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ (COP32) ወደ አዲስ አበባ ማምጣት ችላለች።
ይሁን እንጂ አዲስ አበባ በአረንጓዴ ጥላዋ ሥር የምታስተናግደው ኮፕ (COP) ጉባኤ ከቴሌቪዥን መስኮት ዜናዎች ጀርባ እጅግ አስደንጋጭና ልብ ሰቃይ ታሪኮችን አዝሏል።
በ1992 በሪዮ ዲ ጄኔሮ ከ100 በላይ የዓለም መሪዎች በተሰበሰቡበት አዳራሽ ሴቨርን ሱዙኪ የተባለች የ12 ዓመት ካናዳዊት ታዳጊ ማይክሮፎኑን ጨብጣ "እንዴት እንደሚጠገን ካላወቃችሁ፣ እባካችሁ ማበላሸታችሁን አቁሙ" ስትል የዓለም መሪዎችን ለስድስት ደቂቃ ያህል አንገት አስደፍታ በጸጥታ አሳስባቸዋለች።
በእነዚህ ጉባኤዎች ውሳኔ የሚተላለፈው በሙሉ ስምምነት (Consensus) በመሆኑ፣ አንዲት ትንሽ ደሴት ከአሜሪካ እና ከቻይና እኩል የድምፅ ጉልበት አላት።
በ2010 በሜክሲኮ ካንኩን ጉባኤ የቦሊቪያው ተደራዳሪ ፓብሎ ሶሎን ብቻቸውን ተቃውሞ በማንሳታቸው የ190 ሀገራት መሪዎችና ዲፕሎማቶች እስከ ንጋቱ 10 ሰዓት ከአዳራሽ መውጣት ተስኗቸው የልዕለ ኃያላን ሀገራት ሚኒስትሮች ኮታቸውን አውልቀው ከታዳጊ ሀገራት ተወካዮች ጋር በወለል ላይ ክብ ሠርተው እስከ መለማመጥ ደርሰዋል።
ከዚያም አለፍ ሲል በ2015 በፓሪስ ጉባኤ ከሁለት ሳምንታት እንቅልፍ አልባ ክርክር በኋላ የፈረንሳዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሎራን ፋቢየስ ዓይናቸው እንባ አቅርሮ ትንሽን አረንጓዴ መዶሻ በመምታት ታሪካዊውን ስምምነት ሲያበስሩ በ2021 ደግሞ የቱቫሉ ደሴት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳይመን ኮፌ እስከ ጉልበታቸው በውቅያኖስ ውኃ ውስጥ ቆመው "እናንተ በአዳራሽ ውስጥ ስትከራከሩ፣ የእኔ ሀገር ግን በውኃ እየሰጠመች ነው" በማለት ዓለምን አስደምመዋል።
በሕይወቷ አንድም ቀን አውሮፕላን ተሳፍራ የማታውቀው የቦረናዋ አርብቶ አደር እናት በኃያላኑ ፋብሪካዎች ጭስ ምክንያት ለነጠፈባት ውኃ "የአየር ንብረት ፍትሕ" የምትጠይቅበት ይህ ታላቅ የሕግና የዲፕሎማሲ መድረክ አሁን አዲስ አበባ ላይ ደርሷል።
የአዳማዋ የአረንጓዴ አሻራ ዘር ከሪዮ ዲ ጄኔሮው የሕግ ዘር ጋር አዲስ አበባ ላይ እንዴት ይገናኛሉ? ኢትዮጵያስ የዓለምን የአየር ንብረት ድርድር ለአንድ ዓመት በፕሬዚዳንትነት ስትመራ ምን ታተርፋለች?
የእነዚህንና የሌሎችንም አነጋጋሪ ጥያቄዎች ሙሉ ታሪካዊ፣ ሕጋዊና ኢኮኖሚያዊ ዳሰሳ ከዝርዝር ትንታኔው ጋር ለማንበብ ሊንኩን ተጭነው ይመልከቱ፦ https://tinyurl.com/ksw5ktzc
በነብዩ ወንድወሰን
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: