ግንቦት 18 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዳማ አፈር በተለመደው የፀደይ ሙቀት እየተሟሟቀ ባለበት በዚያች ዕለት፣ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲና የአካባቢ ጥበቃ ታሪክ የቀየረ አንድ ታሪካዊ ክስተት ተፈጠረ። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታሪካዊውን የችግኝ ተከላ ለማስጀመር ወደ መሬት ከማጎንበሳቸው በፊት፣ በወቅቱ ለብዙዎች የማይደረስ የመሰለውን ታላቅ ራዕይ በአጭር ግን ታሪካዊ ዓረፍተ ነገር እንዲህ ሲሉ አበሰሩ፦«ዛሬ አምስት ሺህ ችግኝ ተዘጋጅቷል። ይሄን አምስት ሺህ ችግኝ በመትከል በጋራ 'ሀ' ብለን ከአራት ቢሊየኑ 5,000 ዛሬ እንቀንሳለን»
ይህንን ቃል ከተናገሩ በኋላ ከጉልበታቸው ዝቅ ብለው፣ እፍኝ አፈር በእጃቸው ዘግነው አንዲት ለጋ ችግኝ ተከሉ። በዚያች ዕለት «ሀ» ተብሎ ከአራት ቢሊዮኑ የተቀነሰችውና አፈር ለብሳ ውኃ የጠጣችው ያቺ ለጋ ቡቃያ፣ ዛሬ ቅርንጫፎቿን አርዝማ ጥላ ወደሚሰጥ ግዙፍ ዛፍነት ተቀይራለች። ይቺ ታሪካዊት ችግኝ ሥሯን በኢትዮጵያ ለም አፈር ውስጥ በጥልቀት ብትሰድም፤ ቅርንጫፎቿ ግን እያደጉ የሄዱት ወደ ዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲ ሰማይ ነበር።
በአዳማ ምድር በ5,000 ችግኞች የተለኮሰው የአረንጓዴ አሻራ፣ ብዙም ሳይቆይ ከመንግሥታዊ መርሐ ግብርነት አልፎ ወደ ጥልቅ የሕዝብ ባህልነት ተሸጋገረ። ከአርሶ አደር እስከ ከተሜ፣ ከሕፃን እስከ አዛውንት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በክረምት ጭቃና በዶፍ ዝናብ ሳይበገሩ ተራራና ሸለቆውን በአረንጓዴ ማዕበል አጥለቀለቁት። በአዳማ ከአራት ቢሊዮኑ ላይ 5,000 በመቀነስ የተጀመረው ጉዞ፣ አራት ቢሊዮኑን አልፎ በበርካታ ቢሊዮን ችግኞች ተጠናክሮ ቀጥሏል። በትናንትናው ዕለት በዜጎች ላብና የጣት አሻራ የተተከሉት እነዚያ ችግኞች፣ ዛሬ ቅርንጫፎቻቸውን አንሰራፍተው የዓለምን መሪዎች በጥላቸው ሥር የሚያሰባስቡበትን ግርማ ሞገስ ያለው የዲፕሎማሲ ካባ ለኢትዮጵያ አጎናጽፈዋታል።
የ«ኮፕ» (COP) ታሪካዊ አመጣጥና የሕግ ምዕራፎች
«ኮፕ» (COP) የሚለው ምህፃረ ቃል "Conference of the Parties" የሚለውን የእንግሊዝኛ ሐረግ የሚወክል ሲሆን፣ በአማርኛ «የቃል ኪዳኑ አባል ሀገራት ጉባኤ» ማለት ነው። ታሪኩ የሚጀምረው የቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ ዓለም በአዲስ ተስፋ በተሞላችበት በ1992 (እ.ኤ.አ.) በብራዚሏ ሪዮ ዲ ጄኔሮ ከተማ ነበር።
በዚያ «የምድር ጉባኤ» (Earth Summit) ተብሎ በሚጠራው ታሪካዊ ስብሰባ ላይ ከ100 በላይ የዓለም መሪዎች ታድመው ነበር። በጉባኤው መካከል ግን አንድ ያልተጠበቀ ክስተት ተፈጠረ። ሴቨርን ሱዙኪ የተባለች የ12 ዓመት ካናዳዊት ታዳጊ ማይክሮፎኑን ጨብጣ በዓለም መሪዎች ፊት ቆመች። «እኔ ገና ልጅ ነኝ፤ ነገር ግን መልሳችሁ መጠገን የማትችሉትን ተፈጥሮ፣ ማፍረሳችሁን እንድታቆሙ ልነግራችሁ መጥቻለሁ» ስትል አዳራሹ በጸጥታ ተዋጠ። ለስድስት ደቂቃዎች የዓለም መሪዎች አንገት ያስደፋው የዚያች ታዳጊ ንግግር፣ የሳይንቲስቶችን ማስጠንቀቂያ የሰው ልጅ የህልውና ጥያቄ አድርጎ አቀረበው። በዚያው ጉባኤ ላይ መሪዎቹ የምድርን ከባቢ አየር ከሙቀት አማቂ ጋዞች ለመታደግ የሚያስችለውን «የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ስምምነት» (UNFCCC) ፈረሙ።
ስምምነቱ በ1994 (እ.ኤ.አ.) ወደ ሥራ ከገባ በኋላ፣ ፈራሚ ሀገራቱ በየዓመቱ እየተገናኙ የገቡትን ቃል መገምገም ጀመሩ። የመጀመሪያው ጉባኤ (COP1) በ1995 በጀርመን በርሊን ሲካሄድ፣ ስብሰባውን የመሩት በወቅቱ ወጣት የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር የነበሩት አንጌላ ሜርክል ነበሩ። ከበርሊኑ ጅማሮ በኋላ ጉባኤው በየዓመቱ ክረምትና በጋ እየተፈራረቀበት ሁለት ታላላቅ የሕግ ምዕራፎችን አስመዝግቧል፦
የ1997ቱ የኪዮቶ ፕሮቶኮል (COP3) እና የእኩለ ሌሊቱ ትግል፦ በጃፓን ኪዮቶ ከተማ የተካሄደው 3ኛው ጉባኤ የመጨረሻ ሌሊት በዲፕሎማሲ ታሪክ አይረሴ ነበር። ተደራዳሪዎች ለ48 ሰዓታት ያለ እንቅልፍ በየኮሪደሩና በየአዳራሹ በነጠላ ቃላትና በአኃዞች ላይ ሲጨቃጨቁ አደሩ። በመጨረሻም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የበለጸጉ የኢንዱስትሪ ሀገራት የሚለቁትን የበካይ ጋዝ መጠን እንዲቀንሱ በሕግ የሚያስገድድ የኪዮቶ ፕሮቶኮል ተወለደ። በወቅቱ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገራት ድህነትን የመዋጋት ቅድሚያ ስለነበራቸው ከዚህ አስገዳጅ ቅነሳ ነፃ ተደርገው ነበር። ይሁንና ግዙፏ በካይ ሀገር አሜሪካ ስምምነቱን አለማጽደቋና እንደ ቻይና ያሉ በፍጥነት በማደግ ላይ የነበሩ ሀገራት ግዴታ ውስጥ አለመካተታቸው የኪዮቶን አቅም አዳከመው።
የ2015ቱ የፓሪስ ስምምነት (COP21) እና አረንጓዴው መዶሻ፦ ከኪዮቶ ክፍተት የተማረው ዓለም፣ በ2015 በፈረንሳይ ፓሪስ ተሰባሰበ። ከሁለት ሳምንታት እልህ አስጨራሽ ድርድር በኋላ፣ የፈረንሳዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሎራን ፋቢየስ ዓይናቸው እንባ አቅርሮ ትንሿን አረንጓዴ መዶሻ አነሱ። «አነስተኛ መዶሻ ብትሆንም፣ ታላቅ ሥራ ትሠራለች» ብለው ጠረጴዛውን ሲመቱ፣ በአዳራሹ የነበሩ የ195 ሀገራት ልዑካን ከመቀመጫቸው ተነስተው እየተቃቀፉ አጨበጨቡ። የፓሪስ ስምምነት «ከላይ ወደ ታች» የሚወርድ ትዕዛዝን አስቀርቶ፣ ሀብታምም ሆኑ ድሃ ሀገራት ሁሉም እንደየአቅማቸው በካይ ጋዝን ለመቀነስ የሚያስችል «በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚወሰን አስተዋጽኦ» (NDC) አዘጋጅተው እንዲያቀርቡ አደረገ። የዓለምን የሙቀት መጠንም ከቅድመ-ኢንዱስትሪ ዘመን አንጻር ከ2 ዲግሪ ሴልሺየስ በታች ለማቆየት፣ ከተቻለም ከ1.5 ዲግሪ ሴልሺየስ እንዳያልፍ የመገደብ ታሪካዊ ግብ አስቀመጠ።
አንዲት ትንሽ ደሴት ልዕለ ኃያላንን የምታስቆምበት ሥርዓት
የኮፕ ጉባኤን ልዩ የሚያደርገው የሕግ አሠራሩ ነው። በ1992 የተፈረመው የUNFCCC ስምምነት በዓለም አቀፍ ሕግ እንደ «እናት ሕግ» (Framework Convention) ያገለግላል። ልክ አንድ የሀገር ሕገ-መንግሥት መሠረታዊ መርሆችን ብቻ አስቀምጦ፣ ዝርዝር ጉዳዮችን ለሚወጡ አዋጆች እንደሚተው ሁሉ፣ ይህም «እናት ሕግ» ጠቅላላ የአየር ንብረት ጥበቃ መርሆችን በማስቀመጥ፣ ዝርዝር የአፈጻጸም ግዴታዎች በየጊዜው በሚፈረሙ ስምምነቶች (እንደ ኪዮቶ እና ፓሪስ) እንዲሞሉ ያደርጋል።
በዚህ ማዕቀፍ ሥር 198 አባላት (Parties) ማለትም 197 ሀገራት እና የአውሮፓ ኅብረት ይገኛሉ። በጉባኤው አዳራሽ ውስጥ ውሳኔ የሚተላለፈው በድምፅ ብልጫ ሳይሆን በሙሉ ስምምነት ነው። ይህ የሕግ አሠራር በጉባኤው ላይ ልብ ሰቃይ ትዕይንቶችን ይፈጥራል። በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚና የጦር ኃይል ሚዛን የትም የማይደርሱ ትናንሽ ሀገራት፣ በኮፕ አዳራሽ ውስጥ ግን ከአሜሪካ እና ከቻይና እኩል የድምፅ ጉልበት አላቸው።
ለአብነትም በ2010 በሜክሲኮ ካንኩን በተካሄደው ጉባኤ (COP16) የቦሊቪያው ተደራዳሪ ፓብሎ ሶሎን ብቻቸውን ተቃውሞ በማንሳታቸው፣ የ190 ሀገራት መሪዎችና ዲፕሎማቶች እስከ ንጋቱ 10 ሰዓት ድረስ አዳራሽ ውስጥ ተቀምጠው መጠበቅ ግድ ሆኖባቸው ነበር። በኮፕ የመጨረሻ ሰዓታት፣ የልዕለ ኃያላን ሀገራት ሚኒስትሮች ኮታቸውን አውልቀውና ክራቫታቸውን አላልተው፣ ከታዳጊ ሀገራት ተወካዮች ጋር በአዳራሹ ወለል ላይ ክብ ሠርተው ሲለማመጡና ሲደራደሩ ማየት የተለመደ ነው።
በዚህ የድርድር ሂደት የሚወጡ ውሳኔዎች በሁለት ይከፈላሉ፦
አስገዳጅ የሕግ ውሎች፦ እንደ ፓሪስ ስምምነት ያሉ፣ በሀገራት ፓርላማዎች ጸድቀው የሀገር ውስጥ ሕግ አካል የሚሆኑና ሀገራት የገቡትን ቃል የመፈጸምና ሪፖርት የማድረግ የሕግ ግዴታ የሚጥሉ ናቸው።
ፖለቲካዊ ውሳኔዎች፦ በየዓመቱ በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ የሚወጡ የድርድር ውጤቶች ሲሆኑ፣ ዋናዎቹን የሕግ ውሎች ወደ ተግባር ለመቀየር የሚረዱ የፋይናንስ እና የአሠራር አቅጣጫዎችን ያስቀምጣሉ።
በእነዚህ ድርድሮች ሁሉ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ዋነኛ የሕግ መከራከሪያ «የጋራ ግን የተለያየ ኃላፊነት» (Common But Differentiated Responsibilities - CBDR) የሚለው መርህ ነው። ይህ የሕግ ቃል በወረቀት ላይ ሲነበብ ደረቅ ቢመስልም፣ በጀርባው ያለው የሰው ልጆች ታሪክ ግን ልብ የሚነካ ነው።
በ2021 በስኮትላንድ ግላስጎው በተካሄደው የCOP26 ጉባኤ ላይ፣ በፓስፊክ ውቅያኖስ የምትገኘው የቱቫሉ ደሴት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳይመን ኮፌ ለጉባኤው ንግግር ያደረጉት ሙሉ ሱፍና ክራቫት ለብሰው፣ እስከ ጉልበታቸው ድረስ በውቅያኖስ ውኃ ውስጥ ቆመው ነበር። መልዕክታቸው ግልጽ ነበር፦ «እናንተ በአዳራሽ ውስጥ ስትከራከሩ፣ የእኔ ሀገር ግን በውኃ እየሰጠመች ነው!»
ይህ እውነታ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ መልኩን ይቀይራል። በቦረና ወይም በሶማሌ ክልል የምትገኝ አንዲት አርብቶ አደር እናት፣ በሕይወቷ አንድም ቀን አውሮፕላን ተሳፍራ አታውቅም፤ የድንጋይ ከሰል የሚያቃጥል ፋብሪካም ላት። ነገር ግን በአውሮፓ፣ በአሜሪካ እና በእስያ ፋብሪካዎች ለሁለት መቶ ዓመታት ወደ ሰማይ የተተፋው ጭስ የዓለምን አየር በማዛባቱ፣ የእሷ ከብቶች የሚጠጡት ውኃ ነጥፏል፤ በደጋው የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኘው አርሶ አደርም የክረምትና የበጋ ወቅት ተዘባርቆበታል።
አፍሪካ ለዓለም በካይ ጋዝ ልቀት ያላት ድርሻ ከ4 በመቶ እንኳን አይበልጥም፤ የአየር ንብረት ለውጥ ዱላ ግን በአህጉሪቱ ላይ ከማንም በላይ ይከብዳል። ስለሆነም «የጋራ ግን የተለያየ ኃላፊነት» የሚለው የሕግ መርህ፣ ከባቢ አየርን የበከሉ የበለጸጉ ሀገራት ለታዳጊ ሀገራት በምጽዋት መልክ ሳይሆን፣ በሕግና በሞራል ግዴታ የአየር ንብረት ፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና ለደረሰው ኪሳራና ጉዳት ማካካሻ እንዲከፍሉ የሚያስገድድ «የአየር ንብረት ፍትሕ» (Climate Justice) መዶሻ ነው።
ከከተሳታፊነት ወደ አስተናጋጅነት፦ የኢትዮጵያ አሻራ እና የCOP32 ትሩፋቶች
ኢትዮጵያ የ32ኛውን የኮፕ ጉባኤ ወደ አዲስ አበባ ማምጣቷ በአንድ ጀምበር የተገኘ ዕድል አይደለም። እ.ኤ.አ. በ2009 በዴንማርክ ኮፐንሃገን (COP15) በነበረው እጅግ ቀዝቃዛ ክረምት፣ የበለጸጉት ሀገራት አፍሪካን ያገለለ ስምምነት በጓሮ በር ለማሳለፍ ሲሞክሩ፣ በዚያ መድረክ አፍሪካ በአንድ ድምፅ እንድትደራደርና በዓመት የ100 ቢሊዮን ዶላር የአየር ንብረት ፋይናንስ ቃል እንዲገባላት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ የማይተካ ሚና ተጫውቷል።
ያ በኮፐንሃገን የተጀመረው የዲፕሎማሲ ዱላ ቅብብሎሽ፣ ዛሬ በተግባራዊ የአረንጓዴ ልማት ታጅቦ አዲስ ምዕራፍ ላይ ደርሷል። ብዙ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ብቻ ሲያወሩ፣ ኢትዮጵያ በ2011 (እ.ኤ.አ.) ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ (CRGE) ስትራቴጂ ነድፋ ወደ ተግባር ገባች።
ይህንን የፖሊሲ ቁርጠኝነት ወደ ሕዝባዊ ንቅናቄ የቀየረው ግን ግንቦት 18 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) «በጋራ ሀ ብለን ከአራት ቢሊየኑ 5,000 ዛሬ እንቀንሳለን» በሚል የመክፈቻ ቃል የተጀመረው «የአረንጓዴ አሻራ» መርሐ ግብር ነው። በዚያች ዕለት ከዚህ ታሪካዊ ንግግር በኋላ በአዳማ ከተተከሉት 5,000 ችግኞች ተነስቶ በመላው ኢትዮጵያ ተራሮችና ሸለቆዎች የተዘረጋው ይህ መርሐ ግብር፣ ዲፕሎማሲውን ከቤተ መንግሥት አውጥቶ የዜጎች የዕለት ተዕለት ተግባር አደረገው። በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞች የተተከሉበት ይህ ንቅናቄ፣ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የንጹሕ ኃይል ልማት እና ከአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻና የኮሪደር ልማቶች ጋር ተዳምሮ፣ ኢትዮጵያን «በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር የምትመራ ሀገር» አድርጎ በዓለም መድረክ አስመስክሯል። ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ (ACS2) በአዲስ አበባ በስኬት ማስተናገዷም ለCOP32 አስተናጋጅነት ሙሉ መተማመንን ፈጥሯል።
ኢትዮጵያ የCOP32 ፕሬዚዳንትነትን ስትረከብ፣ ለአንድ ዓመት የዓለምን የአየር ንብረት ድርድር ትመራለች። ይህም፦
የአፍሪካን የፋይናንስ፣ የአረንጓዴ ኃይል እና የግብርና አጀንዳዎች የዓለም ቀዳሚ ትኩረት እንዲሆኑ ያስችላል።
ለሁለት ሳምንታት ወደ አዲስ አበባ የሚጎርፉት በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ልዑካን፣ ጋዜጠኞች እና ተመራማሪዎች ለኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ለሆቴሎች፣ ለትራንስፖርት እና ለባህል ኢንዱስትሪው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ያስገኛሉ።
የሀገሪቱን የታዳሽ ኃይል እና የካርቦን ገበያ ፕሮጀክቶች ለዓለም አቀፍ ባለሀብቶች እና የፋይናንስ ተቋማት በቀጥታ የምትሸጥበት የገበያ አደባባይ ይሆናል።
በአረንጓዴ መናፈሻዎች፣ በዘመናዊ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶች እንዲሁም በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እየተዋበች ያለችው አዲስ አበባ፣ የዓለም የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከልነቷን በተግባር የምታረጋግጥበት የገጽታ ግንባታ መድረክ ይሆናል።
በCOP32 ወቅት በአዲስ አበባ የስብሰባ አዳራሾች ውስጥ የኢትዮጵያ ቡና መዓዛ ከዓለም አቀፍ የሕግ ሊቃውንት የጦፈ ክርክር ጋር ሲዋሃድ፣ ይህ ታሪካዊ አጋጣሚ የመንግሥት ዲፕሎማቶች ብቻ የሚሳተፉበት ኩነት ተደርጎ ሊታይ አይገባም። መገናኛ ብዙኃን ከፕሮቶኮል ዜናዎች ባለፈ የድርድሩን ሕጋዊና ኢኮኖሚያዊ አንድምታዎች ለሕዝብ የማስረዳት፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ተመራማሪዎች ሀገራዊ የጥናት ውጤቶችን በዓለም አቀፍ መድረኮች የማቅረብ፣ ወጣቶችና የግሉ ዘርፍ ደግሞ የአረንጓዴ ፈጠራ ሥራዎቻቸውን ለዓለም የማስተዋወቅ ታሪካዊ ኃላፊነት አለባቸው።
ከሠላሳ ዓመታት በፊት በሪዮ ዲ ጄኔሮ የተዘራው የዓለም የአየር ንብረት ሕግ ዘር፣ ግንቦት 18 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ «ሀ» ተብሎ በ5,000 ችግኞች ከተጀመረውና ዛሬ ኢትዮጵያን በአረንጓዴ ልብስ ካጎናጸፋት የአረንጓዴ አሻራ ጋር አዲስ አበባ ላይ ይገናኛል። ዓለም ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ፣ ሀገራችን እንግዳ ተቀባይነቷን ብቻ ሳይሆን፣ የአፍሪካን የአየር ንብረት ፍትሕ ጥያቄና የአረንጓዴ ልማት ተስፋ በዓለም አደባባይ በድል የምታስተጋባበት ታላቅ የታሪክ ምዕራፍ እውን ሆኗል።
ስለ ጉባኤው አሁናዊ መረጃዎች እና ዝግጅቶች ሙሉ መለዕክቶችን ለማግኘት ሁልጊዜም ትክክለኛው የኮፕ 32 ይፋዊ ድረ-ገጽ (Official COP32 website) በመጎብኘት መከታተል ይቻላል።
በነብዩ ወንድወሰን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: