Search

ኢትዮጵያ ከአረንጓዴ ዐሻራ እስከ ካርበን ንግድ

ሰኞ ጥቅምት 30, 2019 84

ኢትዮጵያ በዝቅተኛ የካርቦን ልቀት፣ በሰፊ የደን ሃብት እና ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ከታዳሽ ሃብት በሚመነጨው የኤሌክትሪክ አቅርቦቷ በዓለም አቀፉ የካርቦን ገበያ ተመራጭነቷን እያሳደገች ይገኛል።

ሀገራችን የአካባቢ ጥበቃን ከኢኮኖሚ ልማት ጋር በማቀናጀት እያከናወነችው ያለው ስራ ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ጭምር በትምህርትነት የሚጠቀስ አርአያ እየሆነ ይገኛል።

ባለፉት ዓመታት በቢሊዮን የሚቆጠር ችግኞችን በመትከል ያከናወነችው ብሔራዊ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በአሁኑ ወቅት ለ"ካርቦን ክሬዲት" አቅርቦት ትልቅ አቅም ፈጥሯል።

በተጨማሪም ከታዳሽ ኃይል የሚመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ለወደፊቱ የካርቦን ንግድ ግዙፍና ተፈላጊ የአቅርቦት አቅም እየፈጠረ ይገኛል።

በዘርፉ ገና በጅምር ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ የመጀመሪያ ከሆኑት ስኬታማ የካርቦን ፕሮጀክቶች መካከል ተጠቃሽ ከሆኑት ከባሌ ተራሮች የደን ጥበቃ እና ከወላይታ ዞን የሁምቦ ወረዳ የተፈጥሮ ደን መልሶ ማልማት ፕሮጀክቶች ተሞክሮ በመውሰድ ማህበረሰቡን ቀጥተኛ ተጠቃሚ ያደረጉ ተጨባጭ ውጤቶችን አስመዝግባለች።

ወደፊት አዳዲስ የካርበን ገበያ አዋጆች ሲተገበሩ እና የዓለም አቀፉ የካርበን ዋጋ በድርድር ሲሻሻል ሀገራችን የምታገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ አረንጓዴ የልማት ራዕይ ከአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ባሻገር በታዳሽ ኃይል ልማት እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶች እና በግብርናው ዘርፍ የአፈር ለምነትንና የውኃ አጠቃቀምን በማሻሻል ረገድ ሰፊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ጉባኤዎች ላይ የአፍሪካን ድምፅ በማስተጋባት ረገድ የላቀ ዲፕሎማሲያዊ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች።

በቱርክ ኮፕ-31 ጉባኤ ላይ ልምዷን የምታካፍለው ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአረንጓዴ ልማት ባከናወነቻቸው ተጨባጭ ስራዎች 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ለማስተናገድ ተመርጣለች።

ይህ ታሪካዊ ዲፕሎማሲያዊ ድል አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ ብቻ ሳትሆን  የመፍትሔው ምንጭ እና ማዕከል መሆኗን የምታሳይበት ወሳኝ መድረክ በመሆኑ፣ ለቀጣይ ትውልድ የሚተርፍ አሻራ ለማስቀመጥ በሀገር ደረጃ ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።

 

በብሌን ደምበሎ

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: