የዛሬው የኢትዮጵያ ትውልድ የትኩረት ማዕከል እና ትልቁ የትግል አውድ የሀገራችንን የኢኮኖሚ ነፃነት ማረጋገጥና የዘመናት ቁጭት የሆነውን የባሕር በር ፍላጎት እውን ማድረግ ነው።
በፍጥነት እያደገ የመጣውን የሕዝብ ቁጥር እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማስቀጠል አስተማማኝና ቀጣይነት ያለው የባሕር በር ማግኘት የዚህ ትውልድ የፍትሕ፣ የእድገት እና የህልውና ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ ቀደም ባሉት ዘመናት በቀይ ባሕር አካባቢ ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ የኖረች ቢሆንም፣ በታሪካዊ አጋጣሚዎች በውስጥ እና በውጭ ኃይሎች ሴራ ወደቦቿን በማጣቷ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በውጭ ወደቦች ላይ ብቻ ጥገኛ ሆና ለመቆየት ተገዳለች።
ይህ ሁኔታም ለሀገራችን ኢኮኖሚ፣ ለንግድ እንቅስቃሴ እና ለብሔራዊ ደኅንነት ከፍተኛ ጫናና ማነቆ በመሆኑ፣ አዲሱ ትውልድ ይህንን ታሪካዊ አደራ በብልሃት ለመወጣት ቁርጠኛ አቋም ይዟል።
ይህንን የዘመናት ጥያቄ ለመመለስ መንግሥት በዲፕሎማሲያዊ መርሆዎች ላይ ተመስርቶ እያደረገ ያለው ጥረት የንግድ ሂደቶችን በማፋጠን፣ የትራንስፖርት ወጪንና ጊዜን በመቀነስ የሀገራችንን የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት ከፍ የሚያደርግ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ እንዳስገነዘቡት፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ማንም ሊክደው የማይችል ፍትሐዊ ጉዳይ እንጂ ሌሎችን የመጉዳት ዓላማ የሌለው ነው።
ኢትዮጵያ የምትፈልገው የባሕር በር ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ በማደግ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ለማጠናከር፣ የንግድ ልውውጥን ለማሳደግ እና የሰላምና መረጋጋት ዋስትናን ለማረጋገጥ ነው።
በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ የባሕር ጠረፍ እና የባሕር ኃይል ያላቸው ሀገራት ያላቸው የድርድርና የፖለቲካ ተሰሚነት ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም ቀጥተኛ የባሕር በር መኖር ኢትዮጵያ በቀይ ባሕርና በስትራቴጂካዊ የውኃ አካላት ዙሪያ በሚደረጉ ውሳኔዎች ላይ ያላትን ድምፅ ከፍ ያደርጋል።
የዓድዋ አባቶች ሀገራቸውን ከቅኝ ግዛት እንዳስጠበቁ ሁሉ፣ የዛሬውም ትውልድ የኢኮኖሚ ነፃነቱን የሚያረጋግጥበትን እና የባሕር በር ባለቤትነቱን የሚያስመልስበትን ታሪክ በዲፕሎማሲ እና በብልሃት በደማቁ ሊጽፍ ይገባል።
በተጨማሪም የባሕር በር ማግኘት የረጅም ጊዜ ብልጽግና እና የሉዓላዊነት መሠረት በመሆኑ፣ አሁን ያለው ትውልድ ውስጣዊ አንድነቱን አጠናክሮ እና የጋራ ትርክትን በጋራ ጥቅም ላይ ገንብቶ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመተሳሰር ታሪካዊ ኃላፊነቱን በብቃት ሊወጣ ይገባል።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: