Search

ጠያቂዋ ሀገር መልስ ሆነች

ሰኞ ጥቅምት 30, 2019 38

ታኅሣሥ 2002 ዓ.ም፤ በታላቁ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ውስጥ የተለየ ሀገራዊ ድባብ ነግሦ ነበር። በዴንማርክ ኮፐንሃገን ለሚካሄደው 15ኛው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP15) የሚያቀናውን የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ለመሸኘት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የሕዝብ ተወካዮች ተሰብስበዋል። በዚያ ታሪካዊ መድረክ ላይ የወቅቱ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ልዑካኑ የተሸከሙትን ከባድ የታሪክ አደራ ሲገልጹ እንዲህ ብለው ነበር፦

«በዛሬው ዕለት እዚህ የምንገኘው የዓለማችን ታላቅ አደጋ የሆነውን የአየር ንብረት መዛባት አሳስቦን በቅርቡ በኮፐንሃገን ከተማ የዓለም እንደራሲዎች በተገኙበት በመፍትሔው ላይ ለመወያየት አፍሪካን ወክለው ለሚሄዱት ወንድሞቻችን መልካም ምኞታችንን ለመግለጽ፣ አፍሪካውያንን፣ የአፍሪካውያንን ስም፣ ያንንም መልእክት ለማስተላለፍና ሕዝባችንም የችግሩን ስፋት እንዲገነዘብ ነው።»

በወቅቱ ልዑካን ቡድኑ በሻንጣው የያዘው የፖሊሲ ሰነድ ብቻ አልነበረም፤ «እኛ ባላመጣነው ጣጣ እየተቀጣን ስለሆነ የአየር ንብረት ፍትሕና ካሳ ይገባናል» የሚል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የድጋፍ ፊርማ ያረፈበት አቤቱታም ነበር። ያኔ በኮፐንሃገን መድረክ ተገኝቶ የአፍሪካን ድምፅ ማሰማት ብቻውን እንደ አንድ ታላቅ ሀገራዊ ዘመቻ ተቆጥሮ፣ በቤተ መንግሥት ደረጃ ክብር ተሰጥቶት ሽኝት ተደርጎለት ነበር።

 

ዛሬ አንዳንድ ወገኖች ኢትዮጵያ 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) በአዲስ አበባ ለማስተናገድ መብቃቷን እንደ ተራ የዲፕሎማሲ መርሐ ግብር አቅልለው ሊመለከቱት ይችላሉ። ይሁን እንጂ የዛሬውን ስኬት ትክክለኛ ክብደት ለመረዳት የ2002ቱን የቤተ መንግሥት የሽኝት ትውስታ መለስ ብሎ ማየት ግድ ይላል። ትናንት በሰው ሀገር መድረክ ላይ ድምፅ ለማሰማት ስትሄድ ይህን ያህል ሀገራዊ ርብርብና ሽኝት ያደረገች ሀገር፣ ዛሬ ታሪክ ራሱን ቀይሮ የዓለም መሪዎችን በራሷ መዲና የምትቀበል አስተናጋጅና የአጀንዳ ቀራጭ መሆኗ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ይህ ሽግግር ከተሳታፊነት ወደ አዘጋጅነት፣ ከተሸኚነት ወደ ጋባዥነት፣ እንዲሁም ከአቤቱታ አቅራቢነት ወደ መፍትሔ አምጪነት የተደረገ ታላቅ የዲፕሎማሲ እጥፋት ነው።

በኮፐንሃገኑ ጉባኤ ወቅት የኢትዮጵያም ሆነ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ትርክት የተቃኘው «በተጎጂነት» ላይ ነበር። የበለፀጉት ሀገራት ለለቀቁት የካርቦን ልቀት አፍሪካ ሰለባ መሆኗን በማስረዳት የካሳና የዕርዳታ ጥያቄ ማቅረብ ዋነኛው ስትራቴጂ ነበር። ባለፉት ዓመታት ግን ኢትዮጵያ የዓለምን ችሮታ ከመጠበቅ ይልቅ፣ በራሷ አቅም ተጨባጭ የአየር ንብረት መፍትሔዎችን መሬት ላይ በማውረድ የዲፕሎማሲ ቋንቋዋን በሦስት ዋና ዋና ጭብጦች ቀይራዋለች፦

የአየር ንብረት ለውጥ መድረኮች ብዙውን ጊዜ በወረቀት ላይ በሚቀሩ የተስፋ ቃላት ቢታሙም፣ ኢትዮጵያ ግን በ2002 ዓ.ም የድጋፍ ፊርማ ያሰባሰበውን ሕዝቧን ወደ ተግባራዊ የአካባቢ ጥበቃ ሠራዊትነት በመቀየር በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን ተክላለች።

ከዚህ ሕዝባዊ ንቅናቄ ጎን ለጎን፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በነፋስ፣ በፀሐይና በጂኦተርማል የኃይል አማራጮች የታገዘው የታዳሽ ኃይል አቅሟ፣ ኢትዮጵያን የቀጣናው የንፁህ ኃይል ማዕከል በማድረግ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲን ከቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስር ጋር በተግባር አዋህዷል። ይህ አረንጓዴ ሽግግር በከተሞችም ተጠናክሮ፣ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች የተከናወኑት የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች፣ ሰፋፊ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶች እንዲሁም በነዳጅ የሚሠሩ የቤት ተሽከርካሪዎችን በማገድ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች (EV) የተደረገው ደፋር የፖሊሲ እርምጃ፣ ከተሜነት ከተፈጥሮ ጋር እንዴት ተስማምቶ እንደሚያድግ የሚያሳይ ዓለም አቀፍ ተምሳሌት አድርጓታል።

ይህንን ተግባራዊ ስኬት ተከትሎ 32ኛው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) በአፍሪካ የፖለቲካ መዲና በአዲስ አበባ መካሄዱ፣ አህጉሪቱ ከምጽዋትና ከአቤቱታ ይልቅ ላበረከተችው ተግባራዊ አስተዋፅኦ የሚመጥን ፍትሐዊ የአየር ንብረት ፋይናንስ፣ የካርቦን ገበያ ተጠቃሚነትና የአረንጓዴ ኢንቨስትመንት በድፍረት እንድትጠይቅ የመደራደሪያ አቅሟን ያጎላዋል።

በጉባኤው የሚታደሙ በሺዎች የሚቆጠሩ ልዑካን፣ ተመራማሪዎችና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ከስብሰባ አዳራሹ ሲወጡ፣ በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት የተፈጠረውን አረንጓዴ ውበት፣ በጎዳናዎቿ የሚመላለሱትን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችና በዙሪያዋ የለሙትን የደን ፓርኮች በዓይናቸው የሚመለከቱ በመሆኑ፣ መዲናዋ የአረንጓዴ ልማት ሕያው የተግባር ማሳያ መድረክ ትሆናለች።

ከዲፕሎማሲያዊ ክብደቱና ከዓለም አቀፍ የገጽታ ግንባታ ትሩፋቱ ባሻገር፣ ጉባኤው የኮንፈረንስ ቱሪዝምን በማነቃቃት ለአየር መንገድ፣ ለሆቴልና ለአገልግሎት ዘርፉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ያስገኛል። በተጓዳኝም የኢትዮጵያን የታዳሽ ኃይልና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ፕሮጀክቶች ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትና ባለሀብቶች ጋር በቀጥታ በማገናኘት፣ ለዘላቂ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ወርቃማ ዕድል ይፈጥራል።

የታሪክ ዑደት አስደናቂ ነው። በ2002 ዓ.ም ኢትዮጵያ በብሔራዊ ቤተ መንግሥቷ ልጆቿን ሰብስባ፣ የሕዝቧን የድጋፍ ፊርማ አስታቅፋ፣ «ድምፃችንን አሰሙልን» ብላ ወደ ኮፐንሃገን ሸኝታ ነበር። ያኔ ዓለም የኢትዮጵያን ድምፅ ለመስማት የፈቀደው በተወሰኑ ደቂቃዎች የመድረክ ንግግር ብቻ ነበር። ዛሬ ግን ኢትዮጵያ ተራሮቿን በደን አልብሳ፣ ወንዞቿን ወደ ብርሃን ቀይራ፣ መዲናዋን በአረንጓዴ ኮሪደር አስውባ ዓለምን ወደ ራሷ ጠርታለች። ትናንት የኮፐንሃገንን በር ያንኳኳችው ኢትዮጵያ፣ ዛሬ በኮፕ 32 የዓለምን መሪዎች በአዲስ አበባ በሯ ላይ ቆማ በኩራት ትቀበላለች፤ ይህ የዲፕሎማሲ ድል የአንድ ትውልድ የልፋት፣ የፖሊሲ ቁርጠኝነትና የታሪክ እጥፋት ሕያው ምስክር ነው።

 

በነብዩ ወንድወሰን

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: