ኢትዮጵያ በሺህ ዓመታት ታሪኳ ውስጥ የነፃነቷን እና የሉዓላዊነቷን አጥር በጀግኖች ልጆቿ ደም እና አጥንት አስከብራ ለዚህ ትውልድ አስረክባለች።
የዛሬው ትውልድ ደግሞ ሁለንተናዊ ከፍታን የማረጋገጥ፣ የኢኮኖሚ ነፃነትን የመቀዳጀት እና የጂኦፖለቲካዊ ህልውናውን የማስከበር ታሪካዊ ጥሪ ቀርቦለታል።
ይህ የዘመናችን ጥሪ በቀጥታ ከቀይ ባሕር መብት እና አደራ ጋር የተሳሰረ ነው።
የቀይ ከባሕር ቀጣና የውኃ አካልነት ወይም መደበኛ የንግድ መስመርነት ባለፈ የሉዓላዊነታችን እውነት፣ የነፃነት ታሪክ፣ የጂኦግራፊያዊ ገጽታ እና የኢኮኖሚ ህልውና ጭምር ነው።
ቀይ ባሕር አውሮፓን፣ እስያን እና አፍሪካን የሚያገናኝ የዓለማችን ዋነኛ የንግድ እና የዲጂታል መስመር ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ95 እስከ 99 በመቶ የሚሆነው የዳታ እና የኢንተርኔት ዝውውር በባሕር ስር ኬብሎች አማካኝነት በዚህ መስመር የሚያልፍ በመሆኑ የቀይ ባሕር ፍላጎታችን ከቀጥታ የንግድ መውጫ ወሰን አልፎ ከዲጂታል ሉዓላዊነት፣ ከብሔራዊ ደኅንነት እና ከቴክኖሎጂ ነፃነት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው።
የመደመር ፍልስፍና የጋራ አቅምን በመጠቀም፣ የታሪክ መዛባቶችን በማስተካከል እና የተሻለችውን የነገዋን ኢትዮጵያ በአስተማማኝ መሠረት ላይ በመገንባት ላይ የተመሰረተ ነው።
የመደመር መንግሥት የቀይ ባሕርን ጥያቄ ወደፊት በማምጣት የተፈጥሮ እና የታሪክ መብትን በዲፕሎማሲያዊ እና በስትራቴጂያዊ አቅም ለማረጋገጥ የሚሄድበት መንገድ፣ የትውልዱን ፍላጎት እና የዘላቂ ልማት ጥቅም ማዕከል ያደረገ ታሪካዊ እርምጃ ነው።
የቀደመው ትውልድ የዳር ድንበር እና ነፃነት አስከብሮ እንዳስረከበው ሁሉ የዚህ ዘመን ትውልድም የባሕር በር ጥያቄ እና የሉዓላዊነት አደራ በዕውቀት፣ በቴክኖሎጂ፣ በዲፕሎማሲ እና በተቀናጀ ጽናት የመመለስ ጥሪ ተደቅኖበታል።
ይህ አደራ በዓለም አቀፍ ሕጎች፣ በፍትሐዊነት፣ በጋራ ዕድገት እና በመደመር እሳቤ ላይ ተመስርቶ ኢትዮጵያን ወደ ታላቅነቷ የሚመልስ የዘመኑ የትውልድ ኃላፊነት ነው።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: