የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የናይጄሪያው ኤር ፒስ (Air Peace) በአፍሪካ አህጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን የአየር ትራንስፖርት ትሥሥር ይበልጥ ለማጠናከር እና ለመንገደኞቻቸው ሰፊ የጉዞ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚያስችላቸውን የሁለትዮሽ የጋራ የበረራ ስምምነት ተፈራርመዋል።
በዚህ የጋራ ስምምነት መሠረት፣ ሁለቱ አየር መንገዶች በመንገደኞች ጉዞ እና በሻንጣ አስተላልፍ አገልግሎት ላይ በጥምረት ይሠራሉ። ስምምነቱ ሁለቱም አየር መንገዶች የሁለቱንም አየር መንገዶች በረራዎች ለሚያካትቱ ጉዞዎች በአንድ ትኬት አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል በመሆኑ፣ መንገደኞች በተለየ ሁኔታ የተቀናጀ እና ምቹ የጉዞ ልምድ እንዲያገኙ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
በዚህም መሠረት መንገደኞች ሙሉ የጉዞ መስመራቸውን በአንድ ትኬት መቁረጥ እና ሻንጣዎቻቸውን የመጨረሻ መድረሻቸው ድረስ በቀጥታ ማስተላለፍ ይችላሉ። ይህም የተለያየ ትኬት የመቁረጥ እና ሻንጣዎችን በየኤርፖርቱ ድጋሚ የመረከብ እና የማስመዝገብ እንግልትን በማስቀረት የጉዞ ሂደቱን ቀልጣፋ ያደርገዋል።
ይህ ስምምነት የኤር ፒስን ሀገር ውስጥ እና ቀጣናዊ የበረራ መረብ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግዙፍ ዓለም አቀፍ የበረራ መረብ (አፍሪካ፣ አውሮፓ፣ እስያ፣ መካከለኛው ምሥራቅ እና አሜሪካ) ጋር ያገናኛል።
በዚህም ከናይጄሪያ እና ከምዕራብ አፍሪካ ዋና ዋና ከተሞች የሚነሡ መንገደኞች በአዲስ አበባ በኩል ወደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች በቀላሉ መጓዝ የሚችሉ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚመጡ ዓለም አቀፍ መንገደኞች ደግሞ በኤር ፒስ የበረራ መረብ አማካኝነት ወደ ናይጄሪያ እና ምዕራብ አፍሪካ ከተሞች የውስጥ በረራቸውን መቀጠል ይችላሉ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ስለ ስምምነቱ በሰጡት አስተያየት፦ “በናይጄሪያ መሪ ከሆነው ኤር ፒስ አየር መንገድ ጋር በዚህ ስትራቴጂያዊ ስምምነት በመጣመራችን እጅግ ደስተኞች ነን” ብለዋል።
ይህ ትብብር የበረራ ትሥሥርን ለማጠናከር፣ የደንበኞችን ምቾት ለማሻሻል እና በመላው አፍሪካ የአየር ጉዞ ዕድገትን ለመደገፍ ያለንን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያንፀባርቅ ነው ሲሉም አክለዋል።
አቅማችንን በማቀናጀት ሰፊ የጉዞ ዕድሎችን በመፍጠር አፍሪካን ከዓለም ጋር ይበልጥ እያቀረብን እንገኛለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
የኤር ፒስ መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አለን ኦንዬማ በበኩላቸው፣ “ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ያደረግነው ይህ አጋርነት የአፍሪካን የአቪዬሽን ትሥሥር ለማጠናከር እና አህጉሪቱን ለማቀራረብ በምናደርገው ጥረት ውስጥ ሌላው ታላቅ ምዕራፍ ነው” ብለዋል።
የኤር ፒስን ሀገር ውስጥ እና ቀጣናዊ መረብ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ተደራሽነት ጋር በማጣመር ወደ አፍሪካ እና ከአፍሪካ ውጭ ለሚደረጉ ጉዞዎች ሰፊ ዕድል መፍጠሩንም ጠቁመዋል።
ይህ ስምምነት በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና (AfCFTA) ማዕቀፍ ውስጥ የሰዎችን፣ የንግድ እና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በማፋጠን ለቀጣናዊ ትሥሥር እና ለኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሎ ይጠበቃል።
በተጨማሪም የቱሪዝም እንቅስቃሴን በማቃለል እና የጉዞ ውስብስብነቶችን በመቀነስ ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወት መሆኑን ከኢትዮጵያ አየር መንገዱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: