ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለአየር ንብረት ለውጥ ዘላቂ ምላሽ ለመስጠት በቱርክዬ አንታሊያ ከተማ እያካሄደ ያለው COP31 ጉባኤ፣ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲዋን ከተሳታፊነት ወደ አዘጋጅነት እና ተግባራዊ አርአያነት መሸጋገሯን ያሳየችበት መድረክ ሆኗል።
የዚህ ታሪካዊ ሽግግር እምብርት ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ‘የመደመር’ ፍልስፍና ነው። ይህ ፍልስፍና ከቱርክዬው ‘ኢሜጄ’ (Imece) ባህላዊ እሴት ጋር ጥልቅ ቅንጅት ያለው ነው።
አንድ አካል ብቻውን ሊወጣው የማይችለውን ከባድ ሸክም ማኅበረሰቡ ተሰባስቦ በጋራ የሚያቀልልበት የቱርክዬው ‘ኢሜጄ’ እሴት እና አቅምን አቀናጅቶ ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዘው ‘መደመር’ ፍልስፍና፣ ዓለም አቀፉን የሰሜን እና ደቡብ ንፍቀ ክበብ (Global North-South) ልዩነት ለማጥበብ ፍቱን መድኃኒት መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ ቱርክዬ ደግሞ በዜሮ-ቆሻሻ ንቅናቄ ባደረጉት ጥረት ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል መሬት ላይ የተመዘገበውን አረንጓዴ ልማት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሳይተዋል።
ኢትዮጵያ በCOP31 ላይ እያሳየች ያለው ተሳትፎ የተመልካችነት ወይም የጥገኛ ተሳታፊነት ሳይሆን፣ የራሷን የሀገር በቀል መፍትሔዎች ለዓለም እያቀረበች ዓለም አቀፉን COP32 በስኬት ለማስተናገድ የምታደርገውን ስትራቴጂያዊ ዝግጅት የሚያሳይ ነው።
ይህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ መድረክ ላይ ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት እና የመፍትሔ አቅራቢነት ሚና በተግባር ያረጋገጠ ሆኗል።
የቱርክዬ የአካባቢ፣ የከተማ ልማት እና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ሙራት ኩሩም ትላንት በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ዓለም የአየር ንብረት ስትራቴጂ ከዚህ በኋላ በተነጠለ መልኩ ሊተገበር እንደማይችል ጠቁመዋል።
ቱርክዬ በአንታሊያ ያቀረበችው ጥሪ መሠረት ያደረገው ‘ኢሜጄ’ የተሰኘውን የቱርክዬ ባህላዊ ሥርዓት እንደሚለው፣ አንድ አካል ብቻውን ሊወጣው የማይችለውን ከባድ ሸክም ማኅበረሰቡ ተሰባስቦ በጋራ የሚያቀልበት የመረዳዳት እሴት ነው።
ይኸው መርሕ የኢትዮጵያን ሀገራዊ የ‘መደመር’ ፍልስፍና — አቅምን በማስተባበር፣ በመደጋገፍ እና በመቀናጀት ውስብስብ ችግሮችን የመፍታት ጥበብ በቀጥታ የሚያንጸባርቅ ነው።
የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ እየተባባሰ በሚገኝበት በዚህ ወቅት፣ የመደመር ትርክት እና የቱርክዬው ‘ኢሜጄ’ የጋራ መርሆችን ማጣመር በሰሜን እና በደቡብ ንፍቀ ክበብ መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ፣ ሀብትን ለማስተባበር እና ከቃል ወደ ተግባር ለመሸጋገር ወሳኝ መሠረት ይፈጥራል።
የሰው ዘር መገኛ፣ የፅናት እና የተስፋ ምድር የሆነችው ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን አየር ንብረት ጉባኤ ለማስተናገድ የምታደርገውን ሀገራዊ እንቅስቃሴ በተመለከተ ሙሉ እና ትክክለኛ የኮፕ-32 ጉባኤ መረጃዎች ከምንጩ ለማግኘት ሁልጊዜም የኮፕ-32 ይፋዊ ድረ-ገጽ https://cop32ethiopia.et/ ይጠቀሙ።
በላሉ ኢታላ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: