አዲስ አበባ አህጉራዊ መቀመጫነቷን ተንተርሳ ለዘመናት የዲፕሎማሲ ማዕከል ሆና አገልግላለች።
ሆኖም ፈጣን የሕዝብ ዕድገት፣ ያረጁ የመሠረተ ልማት አውታሮች እና ያልተቀናጀ የከተማ ማስፋፋት ለረጅም ዓመታት የመዲናዋን ተወዳዳሪነት እና የነዋሪዎቿን የኑሮ ጥራት ሲፈታተኑ ቆይተዋል።
አሁን ላይ የተጀመረው የኮሪደር ልማት አዲስ አበባን በቀጣናው ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ዘመናዊ ከተሞች ጋር የሚያስተካክላትን ታላቅ የከተማ ትራንስፎርሜሽን እውን እያደረገ ይገኛል።
የኮሪደር ልማቱ ቀደም ሲል የነበሩትን የተበታተኑ የመሠረተ ልማት ሥራዎች በማቀናጀት አጠቃላይ የከተማ ውበትን እና አገልግሎትን ማዕከል ያደረገ አቀራረብን የተከተለ ነው፡፡
በዚህም ሰፋፊ የመኪና መንገዶች፣ የተለዩ የብስክሌት መስመሮች እና ምቹ የእግር መንገዶች ተገንብተዋል። ይህም የትራፊክ እንግልትን ከመቀነሱም በላይ የሕዝብ ትራንስፖርት ፍሰትን አቀላጥፏል።
በመሠረተ ልማት ረገድም የፍሳሽ ማስወገጃ፣ የኤሌክትሪክ እና የቴሌኮም መስመሮች በመሬት ስር የተቀናጀ አደረጃጀት እንዲኖራቸው ተደርጓል።
በተጨማሪም መዲናዋን ለነዋሪዎች እና ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ ሰፋፊ የሕዝብ መዝናኛ ፓርኮች፣ የውኃ ፋውንተኖች፣ የሕዝብ አደባባዮች እና አረንጓዴ ስፍራዎች በመንገድ ዳርቻዎች እንዲስፋፉ ተደርጓል።
የኮሪደር ልማት ከመሠረተ ልማት ማሻሻያነት አልፎ የመዲናዋን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚያነቃቃ ዋና ሞተር ነው።
ለንግድ ተቋማት፣ ለሆቴሎች እና ለሪል እስቴት አልሚዎች አዲስ የዕድገት መስኮት ከፍቷል።
አዳዲሶቹ ፓርኮች፣ የታሪክ እና የባህል ማዕከላት ከአጠቃላዩ የልማት እንቅስቃሴ ጋር ተዳምረው አዲስ አበባን የኮንፈረንስ ቱሪዝም (MICE) እና የዕረፍት ጊዜ መዳረሻ አድርገዋታል።
እንዲሁም በግንባታው ወቅት ከተፈጠሩት ጊዜያዊ ሥራዎች ባሻገር በተስፋፉ የንግድ እና የአገልግሎት ዘርፎች ዘላቂ የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል።
ነዋሪዎች ከቤታቸው ወጥተው የሚዝናኑባቸው እና ስፖርት የሚሠሩባቸው ነፃ የሕዝብ ቦታዎች መበራከታቸውም የአካል እና የአዕምሮ ጤናን ያጠናክራል።
የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ከተማዋን ከድሮው የኮንክሪት እና የትራፊክ መጨናነቅ ገጽታዋ አውጥቶ ወደ ዘመናዊ፣ አረንጓዴ እና ለኑሮ ምቹ ከተማነት እየቀየራት ይገኛል።
ተግዳሮቶቹን በማመጣጠን እና አካታች የከተማ ዕድገትን በመከተል አዲስ አበባ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን ብቻ ሳይሆን በአህጉሪቱ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀደምት ዘመናዊ እና ተወዳዳሪ ከተማ የመሆን ራዕይዋን በተግባር እያረጋገጠች ትገኛለች።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: