Search

የኢትዮጵያ ባሕር በር ጥያቄ ምላሽ ማግኘት የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው፡- ትውልደ ኤርትራዊው ንጉሰለተብረሃን ሱልጣን

ማክሰኞ ኅዳር 01, 2019 96

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ ማግኘት የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ትውልደ ኤርትራዊው ንጉሠለተብረሃን ሱልጣን ገልጿል።

ትውልደ ኤርትራዊው ንጉሠለተብረሃን ከኢቲቪ ጋር ባደረው ቆይታ፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በባሕሩ ያላትን ታሪካዊ፣ ጂኦግራፊያዊ እና ፖለቲካዊ መብት በመሆኑ ህጋዊ ይዞታዋን “ይገባኛል” ሳይሆን “ይመለስልኝ” የሚል መሆን እንዳለበት አስረድቷል።

የኤርትራ ሕዝብ አሁን ባለው ሁኔታ ከባሕሩ ምንም ዓይነት ጥቅም እንደማያገኝ ገልጾ፣ ሕህዝቡ ዓሣ አጥምዶ ለምግብ ዋስትናው መጠቀም፣ በነጻነት መንቀሳቀስ እና መነገድ ካልቻለ የባሕር በሩ ለኤርትራውያን ምንም ፋይዳ እንደሌለው ጠቁሟል። የአሰብ ወደብ በጋራ ኃላፊነት ሊለማ እንደሚገባም ገልጿል።

አሁን ላይ የኢትዮጵያ ማንነትንና ሐሳብን ማዕከል አድርጎ የተነሳው የመደመር መንግሥት፣ በመደመር እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ቀጣናዊና አህጉራዊ ተጽዕኖውን እያሳደገ እንደሚገኝ አመላክቷል።

ትውልደ ኤርትራዊው በልጅነት ትዝታቸው የነበሩትን የወደብ ከተሞች ድባብ እና አሁናዊ አሳዛኝ ሁኔታ በማስታወስ፣ የኤርትራ ከኢትዮጵያ መገንጠል ያመጣውን ውድቀት በቁጭት አንስቷል።

በስልጣን ጥማት የታወረው ሻዕቢያ በነጻነት ስም የግብጽን አጀንዳ ተሸክሞ ኤርትራን የውጭ ኃይሎች መጫወቻ እያደረጋት እንደሚገኝ በመግለጽ፣ የግብጽ የጂኦ-ፖለቲካ ሴራ በኢትዮጵያ ውድቀት ላይ ያነጣጠረ መሆኑን እና ኤርትራን ከኢትዮጵያ በመገንጠል ረገድ ዋነኛ መሃንዲስ መሆኗን ተናግሯል። የዚህ መራራ ታሪክ የመጀመሪያ ተጎጂ ግን ራሱ የኤርትራ ሕዝብ መሆኑንም አስገንዝቧል።

በፌዴሬሽን ከእናት ሀገር ኢትዮጵያ ጋር ከተቀላቀሉ  ጀምሮ የነበሩ ችግሮች የውጭ ኃይሎች ሴራ ውጤት መሆናቸውን ተናግሯል።

ዛሬ ላይ የኤርትራ ሕዝብ በስደት ላይ እንደሚገኝ እና ሀገሩ ውስጥ ሰላም እና እፎይታ እንዳጣ በመጥቀስ፣ የግብጽ እና ተላላኪዎቿ ሰርክ ተግባር ኢትዮጵያን ከባሕር በር አርቆ በኢኮኖሚ እና በጸጥታ የማዳከም ምኞት ብቻ መሆኑን አጽንኦት ሰጥቷል።

 

በመሐመድ ፊጣሞ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: