የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በCOP31 በአንታሊያ ከአፍሪካ ልማት ባንክ የአየር ንብረት ለውጥ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አንቶኒ ኦኮን ንዮንግ እና የGlobal Covenant of Mayors አምባሳደር እና የፓሪስ ቀድሞ ከንቲባ አን ሂዳልጎ ጋር ተወያይተዋል።
ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ውይይታቸው በአዲስ አበባ የአየር ንብረት እና ዘላቂ የከተማ ልማት ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም የአየር ንብረት ፋይናንስን በቀጥታ ለከተሞች ማድረስ፣ የፕሮጀክት ዝግጅትና አፈጻጸም አቅምን ማጠናከር እንዲሁም በአረንጓዴ ልማት፣ በወንዝ ዳርቻ ልማት፣ በከተማ መልሶ ማልማትና በከተማ ግብርና የተገኙ ልምዶችን ለመማማርና ለመለዋወጥ የሚያስችሉ የትብብር መስኮችን ለማጠናከር ተስማምተናል ብለዋል።
አዲስ አበባ የCOP32 አስተናጋጅ ከተማ በመሆኗ፣ የአፍሪካ ከተሞችን የጋራ የአየር ንብረት ቅድሚያዎች፣ የፋይናንስ ፍላጎቶች እና የልማት አጀንዳ በአንድ ድምፅ ለዓለም ማቅረብ የሚያስችል መድረክ ለመፍጠር ትልቅ እድል እንዳላትም አመላክተዋል።
የጋራ ድምፃችንን በማጠናከር፣ የአፍሪካ ከተሞችን የልማት ፍላጎት፣ የፋይናንስ ተደራሽነት እና የቴክኖሎጂ ትብብር እናሳድጋለን ሲሉም አክለዋል።
የሰው ዘር መገኛ፣ የፅናት እና የተስፋ ምድር የሆነችው ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን አየር ንብረት ጉባኤ ለማስተናገድ የምታደርገውን ሀገራዊ እንቅስቃሴ በተመለከተ ሙሉ እና ትክክለኛ የጉባኤውን መረጃዎች ከምንጩ ለማግኘት ሁልጊዜም የኮፕ-32 ይፋዊ ድረ-ገጽ https://cop32ethiopia.et/ ይጠቀሙ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: