Search

ግብፅ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራትን ፍላጎት አክብራ አታውቅም፡- ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)

ማክሰኞ ኅዳር 01, 2019 91

የኢትዮጵያን ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ማፋጠን፣ የውጭ ንግድ ፍሰትን ማሳደግ እና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የባሕር በር ባለቤትነትን ማረጋገጥ ከመደመር ታላቁ ስትራቴጂ አንዱ እና ዋነኛው አካል መሆኑን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ የማልማት የዘመናት ቁጭት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እውን በማድረግ ታሪክ ጽፋለች።

በአሁኑ ወቅት ደግሞ የባሕር በር ባለቤትነት ታሪካዊ ጥያቄዋን ምላሽ ለማግኘትና ለማረጋገጥ እየሠራች እንደምትገኝ ተናግረዋል። 

ይህ ጉዳይ ለዘመናት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ሲነሳ የኖረ ምላሽ ያላገኘና በሀገራዊ ቁጭትነት የቆየ ታሪካዊ ጥያቄ መሆኑን አንስተው፣ ኢትዮጵያ የባሕር በር መውጫዋን ማጣቷ በሀገራችን የታሪክ፣ የፖለቲካና የብሔራዊ ጥቅም ጉዞ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳረፈ ክስተት መሆኑን አመላክተዋል።

በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ አመራር የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም እና የሕዝቡን ጥያቄዎች አሳልፎ ለታሪካዊ ጠላቶች መስጠቱ በታሪክ ትልቁ ጠባሳ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በመንግሥት ላቅ ያለ የዲፕሎማሲ አካሄድ ኢትዮጵያ የባሕር በር ይገባታል የሚለው እሳቤ ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጉዳይ እየሆነ መምጣቱን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ እንዳትገነባ በታሪካዊ ጠላቶቻችን የተፈጸመው ደባ በአንድነታችን እንደመከትነው ሁሉ አሁንም በሴራ ያጣነውን የባሕር በር በአንድነታችን አረጋግጠን የኢትዮጵያን ሥልጣኔ በከፍታ ላይ እንገነባለን ብለዋል።

ኢትዮጵያ አሁን የምትከተለው ሥልጡን አካሄድ ከወቅታዊ ፍላጎት ባለፈ የመጪዎቹን ትውልዶች ዕድል የሚወስን ስትራቴጂያዊ አቅጣጫ መሆኑን ጠቅሰው፣ የመደመር ታላቁ ስትራቴጂም በ2050 ብልፅግናዋን ያረጋገጠች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከበረችና የተፈራች ሀገር መገንባትን ዓላማ ማድረጉን አብራርተዋል።

ይህ ስትራቴጂ የዛሬን ችግሮች ብቻ ለመፍታት ሳይሆን የነገውን ትውልድ የልማት፣ የኢኮኖሚ እና የሉዓላዊነት ፍላጎቶች ታሳቢ ማድረጉንም ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ በራሷ ሉዓላዊ ግዛት ውስጥ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶቿን በአግባቡ ማልማት፣ የዓባይን ወንዝ ጨምሮ ያሏትን ሀብቶች ለሕዝቦቿ ብልፅግና ማዋልና የሀገራችን የኢኮኖሚ አቅም ማሳደግ ዋነኛ የልማት አቅጣጫዎች አድርጋለች ብለዋል።

የባሕር በር ባለቤትነትን የማረጋገጥ ጉዳይም የዚሁ ስትራቴጂ አንዱ አካል መሆኑን አስረድተዋል።

ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላትና በሕዝብ ብዛት ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገራት መካከል የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ የባሕር መውጫ አለመኖሩ በንግድ፣ በትራንስፖርትና በኢኮኖሚያዊ ትሥሥር ላይ የሚፈጥረው ጫና ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ስለሆነም የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄዋ በሕጋዊ፣ በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍትሔ ማግኘቱ ለሀገራችን የወደፊት እድገት ወሳኝ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ግብፅ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራትን ፍላጎት አክብራ አታውቅም ያሉት ሚኒስትሩ፣ ከተላላኪዎቿ ጋር ኢትዮጵያ በድህነት ውስጥ እንድትቆይ ፍላጎታቸው መሆኑንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ የዓባይን ውሃ የማልማት ታሪካዊ ቁጭቷን በተግባር እንዳረጋገችው ሁሉ፣ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄዋንም በሀገራዊ አንድነት፣ በጠንካራ ዲፕሎማሲና በሕጋዊ አካሄድ ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: