Search

የቢሾፍቱው ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያ እና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር

ማክሰኞ ኅዳር 01, 2019 101
የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያን አጠቃላይ መዋቅራዊ ሽግግር ውስጥ ለማስገባት የያዘው ራዕይ በአሁኑ ወቅት በኮሪዶር ልማት፣ በኢንዱስትሪ፣ በግብርና እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጨባጭ ፍሬዎችን እያፈራ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ማስጀመርያ ላይ “የዛሬ 10 ዓመት የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሁለቱም ምዕራፎች እና በርካታ የጀመርናቸው ታላላቅ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚውን ኢኮኖሚ ትገነባለች” በማለት ያደረጉት ንግግር የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ የሚያመላክት ነው።
በዓመት ከ100 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ይዞ የሚገነባው ይህ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት እና የሎጂስቲክስ ዋና ማዕከል ያደርጋታል።
ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ከአየር መንገድ ዕድገት ባለፈ የቱሪዝም ፍሰትን በአስደናቂ ሁኔታ ይጨምራል፤ የወጪ ንግድን እና የሸቀጦችን ፈጣን ዝውውር ያፋጥናል፤ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ የሥራ እድሎችን በመፍጠር የቀጣናውን ኢኮኖሚ ያነቃቃል።
ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ ኢኮኖሚ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ዐበይት ሥራዎች በበርካታ ዘርፎች የተከፋፈሉ ናቸው።
በኮሪዶር እና መሠረተ ልማት ግንባታ የከተሞችን ውበት እና ለኑሮ ምቹነት ማሳደግ፣ የንግድ መስመሮችን ማገናኘት እና የትራንስፖርት ፍሰትን ዘመናዊ ማድረግ ዋነኞቹ ናቸው።
በግብርናው ዘርፍ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከመሸፈን አልፎ ምርትን ለውጭ ገበያ ማቅረብ እና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ተችሏል።
በኢንዱስትሪ እና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ደግሞ የ“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄን በመምራት የሀገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ እና የውጭ ምንዛሪን መቆጠብ ሌላኛው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው።
ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንዲሁም ከንፋስ እና ፀሐይ ኃይል ፕሮጀክቶች ለሀገር ውስጥ እና ለጎረቤት ሀገራት ኤሌክትሪክ ማቅረብ ተጀምሯል።
ከዚሁ ጎን ለጎን የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶችን በማስፋፋት የፋይናንስ ተደራሽነትን ማሳደግ እየተከናወኑ ከሚገኙ ዐበይት ተግባራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
ኢትዮጵያ የጀመረችው አጠቃላይ የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ የግል ዘርፉን ለማበረታታት እና የገንዘብ ሥርዓቱን ዘመናዊ ለማድረግ የተነደፈ ነው።
በተጨማሪም የሥራ ፈጠራን እና የቴክኖሎጂ ጀማሪ (ስታርት አፕ) ድርጅቶችን ለመደገፍ የተዘረጉ አሠራሮች ወጣቱ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በግንባር ቀደምትነት እንዲመራ ዕድል ፈጥረዋል።
የዛሬ 10 ዓመት ሙሉ በሙሉ የሚጠናቀቁት እንደ ቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ተነጥለው የሚታዩ አይደሉም።
ይልቁንም ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ፣ በቴክኖሎጂ እና በማኅበራዊ ልማት ሙሉ በሙሉ ወደተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግሩ የመደመር ራዕይ አካላት ናቸው።
በአድማሱ አራጋው
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: