ተለዋዋጭ የአየር ጠባይ በግብርና እና በዜጎች ኑሮ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት አስቀድሞ ለመከላከል፣ የሳተላይት መረጃን እና ሰው ሠራሽ አስተውሎትን (AI) ያቀናጀ ዘመናዊ ሥርዓት እየተተገበረ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
በቱርክዬ አንታሊያ ከተማ ‘ከቃላት ባለፈ ወደ ተግባርና አፈጻጸም መሸጋገር’ በሚል መሪ ሃሳብ 31ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ31) እየተካሄደ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኮፕ 31 ጉባኤ ባደረጉት ንግግር፤ የኤል ኒኞ ክስተት የሚያስከትለው ተደጋጋሚ ድርቅና ጎርፍ ምርትን እንደሚጎዳና ቤተሰቦችን ከቀዬአቸው እንደሚያፈናቅል አንስተው፣ አደጋው ካለፈ በኋላ ማገገም እጅግ ረጅም ጊዜ ስለሚወስድ በቴክኖሎጂ የታገዘ የቅድመ መከላከል ሥራ ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረዋል።
በዚህም የመሬት ሁኔታን በሳተላይት በመከታተልና የአየር ትንበያዎችን በሰው ሠራሽ አስተውሎት በማሻሻል ለአርሶ አደሮች ወቅታዊ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠ ነዉ ብለዋል፡፡
‹‹ፋይዳ›› ዲጂታል መታወቂያ ደግሞ ድጋፍ የሚሹ ቤተሰቦችን በፍጥነትና በትክክል ተደራሽ ለማድረግ እያገዘ መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የአየር ንብረት ደኅንነት ከድንበር ባሻገር ለዓለም ገበያ ቀጥተኛ ትርጉም እንዳለው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችውና በዝናብ ውኃ የሚለማው የአረቢካ ቡና በሙቀት መጨመርና በዝናብ መዛባት ሳቢያ የሚበቅልባቸው ደኖችና እርሻዎች ለአደጋ ተጋለጭ መሆናቸዉን አስጠንቅቀዋል።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: