በቱርክዬ አንታሊያ እየተካሄደ በሚገኘው 31ኛው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP31) ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጠንካራ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዋና ፀሐፊው በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በቁርጠኝነት የተወሰዱ እርምጃዎች እና የበለጸጉ ሀገራት በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት የሚያደርጉት ድጋፍ በፈጠራና በቴክኖሎጂ የታገዘ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
የአየር ንብረት ቀውሱ ከሰው ልጅ ጥረት በላይ እየፈጠነ በመሆኑ የዓለም መሪዎች አፋጣኝ እና ቁርጠኛ እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2025 የተመዘገበው የጋዝ ልቀትና የሙቀት መጠን ከምንጊዜውም በላይ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን የጠቆሙት አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤ ከቅሪተ አካል ነዳጆች (ከሰል፣ ዘይት እና ጋዝ) ወደ ንጹህ ኢነርጂ የሚደረገውን ሽግግር ማፋጠን እንደሚገባ አሳስበዋል።
በንግግራቸውም የቅሪተ አካል ነዳጅ ተሟጋች ቡድኖች ወሳኝ የአየር ንብረት እርምጃዎችን እያዘገዩ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ «የቅሪተ አካል ነዳጆች እንደ ዳይኖሰሮች መጥፋት አለባቸው፤ ዳይኖሰሮች ለጥቅማቸው የሚሟገት ቡድን አልነበራቸውም፣ እነዚህ ግን አሏቸው» ሲሉ አስገንዝበዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ከሀገራት የምላሽ ዝግጅት ጋር እንደማይጣጣም ገልጸው፤ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ያሳዩት መዘናጋት ዓለምን ለአደጋ እያጋለጣት በመሆኑ የተቀናጁ አፋጣኝ እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በጉባኤው በንጹህ የኢነርጂ ሽግግር፣ በአረንጓዴ የኢንዱስትሪ ልማት፣ በአየር ንብረት ፋይናንስ፣ በፓሪስ ስምምነት ትግበራ እና በከተሞች የመቋቋም አቅም ላይ ሰፊ ትኩረት የተደረገ ሲሆን፤ ከዚሁ ጎን ለጎን እንደ ሚቴን ያሉ አደገኛ ብክለቶችን መቀነስ የአጭር ጊዜ የሙቀት መጨመርን ለማዘገየት ወሳኝ በመሆኑ የካርቦን እና የግሪንሀውስ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ የሚደረጉ ጥረቶች ሊጠናከሩ እንደሚገባ ተገልጿል።
በልዩ እሸቱ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: