Search

አረንጓዴ ዛፍን የቆረጠ ራሱን እንዳጠፋ ይቆጠራል፡- ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን

ረቡዕ ኅዳር 02, 2019 73

በቱርክዬ አንታሊያ እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ (COP31) ላይ ንግግር ያደረጉት የቱርክዬ ፕሬዚዳንት ረጅብ ጣይብ ኤርዶጋን ተፈጥሮን እና አካባቢን መጠበቅ ከሀገራቸው የሥልጣኔ እምብርት ጋር የተያያዘ ቅዱስ አደራ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንቱ አባቶቻቸው የዛፍን ሕይወት ከሰው ሕይወት ጋር በማነጻጸር "አረንጓዴ ዛፍን የቆረጠ ራሱን እንዳጠፋ ይቆጠራል" ይሉ እንደነበር በማስታወስ የተፈጥሮን ከፍተኛ ዋጋ አጉልተዋል።

"እኛ ጉንዳንን እንኳ መጉዳት እንደ ኃጢአት የምንቆጥር እንዲሁም ነገ የቂያማ ዕለት መሆኑን ቢያውቅ እንኳ በእጁ ያለችውን የመጨረሻዋን ችግኝ መትከል አለበት በሚለው መርሕ የምንመራ ሕዝቦች ነን" ብለዋል።

እንጀራን እንደ በረከት፣ ውኃን እንደ ቅዱስ፣ ዛፍን ደግሞ እንደ ሕይወት የሚቆጥረው ባህላቸው ለአካባቢ ጥበቃ እና ለአየር ንብረት ፖሊሲዎቻቸው ዋና መመሪያ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ቱርክዬ የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት በሚደረጉ ዓለም አቀፍ ጥረቶች የችግሩ አካል ሳይሆን የመፍትሔው አካል ለመሆን እየሠራች መሆኗን ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት ከኃይል እስከ ኢንዱስትሪ፣ ከትራንስፖርት እስከ ግብርና ባሉት ሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች አረንጓዴ ሽግግርን ተግባራዊ እያደረገች መሆኑን አብራርተዋል።

ቱርክዬ የታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንቶችን እያሳደገች እና የንጹሕ ትራንስፖርት መፍትሔዎችን እያፋጠነች መሆኗን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ከተገነባው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ አቅም ውስጥ የታዳሽ ኃይል ምንጮች ድርሻ ከ60 በመቶ በላይ መድረሱን አረጋግጠዋል።

ለፈረንጆች 2053 ዓ.ም የያዙትን የተጣራ ዜሮ የጋዝ ልቀት (net-zero emissions) ግብ ለማሳካት አዲስ የወጣውን የአየር ንብረት ሕግ ጨምሮ ተቋማዊ መሠረቶቻቸውን በማጠናከር የአረንጓዴ ልማት ጉዟቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

 

በመሐመድ ፊጣሞ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: