ኢትዮጵያ የአየር ንብረት እርምጃን የኢኮኖሚ ፖሊሲዋ ዋና አካል በማድረግ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤን፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂን እና የታዳሽ ኃይል አጠቃቀምን አጣጥማ እየሠራች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ31ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP31) ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የመደመር ፍልስፍና ሰዎችን፣ ተቋማትን እና ሀብትን ለአንድ የጋራ ዓላማ በማስተባበር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
በዚህም መሠረት በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በሚሳተፉበት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እስከ አሁን ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን አብራርተዋል።
ይህም የተጎዱ መሬቶችን በማንሰራራት፣ የደን ሽፋን በመጨመር፣ የአካባቢ ጥበቃን የቤተሰብ ባህል በማድረግ እና ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ አዎንታዊ ለውጥ ማምጣቱን ጠቅሰዋል።
ይህን የተፈጥሮ እንክብካቤ ሥራ ወደ ከተሞችም በማስፋፋት የጎርፍ መከላከያዎችን መገንባት፣ የተበከሉ ወንዞችን ማጽዳት እና የወንዝ ዳርቻዎችን ለህፃናትና ለቤተሰቦች መዝናኛነት የሚያገለግሉ ፓርኮችና የእግር መንገድ የማድረግ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በኢነርጂ ዘርፍ በኩል ኢትዮጵያ የነዳጅ ተሽከርካሪዎችን ማስገባት በመከልከል ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች (EVs) ሙሉ በሙሉ ሽግግር እያደረገች መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም ሀገራችን ልቀትን ለመቀነስ የምታደርገውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አክለውም ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቷ 90 በመቶ ያህሉን ከውኃ የምታመነጭ እና ለጎረቤት አገራትም የምታሰራጭ ብትሆንም፤ ድርቅ በሚከሰትበት ጊዜ በኢኮኖሚው ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የዘላቂ ኃይል አማራጮችን በማስፋፋት ላይ ትገኛለች።
በዚህም መሠረት የነፋስ፣ የፀሐይ፣ የጂኦተርማል እና ለወደፊቱ የሚያገለግል የኒውክሌር ኃይል ልማት እቅዶች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው።
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን ቀድሞ ለመከላከል እና ለመቋቋም ቴክኖሎጂ ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሳተላይት መረጃዎችን እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሎጂን በመጠቀም የአየር ሁኔታ ትንበያዎችን በማሻሻል ለአርሶ አደሮች የቅድመ-ማስጠንቀቂያ መረጃዎች እየቀረቡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: