Search

ኢትዮጵያ በቤቶች ልማት ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ላይ ነች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ዓርብ ኅዳር 04, 2019 71

ኢትዮጵያ በቤቶች ልማት ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ላይ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመርካቶ (ቅጠል ተራ) አካባቢ ያለውን የቤቶች የልማት እንቅስቃሴ በተመለከቱበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ የቤት ልማት ሥራው በጥቂት ጊዜ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ጠቁመዋል።

በከተሞችም ሆነ በገጠሮች ሰፊ የቤት ፍላጎት መኖሩን አንስተው፣ አርሶ አደሮች ከብቶች ጋር ከሚኖሩበት አስቸጋሪ አኗኗር ለመላቀቅ የ"ገጠር ኮሪደር" መጀመራቸውን አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያ ከተሞች እና ገጠሮች እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት እና የቤት ግንባታ ሥራዎች የዜጎችን የኑሮ ደረጃ የሚቀይሩ እና ተስፋ ሰጪ ጅምሮች መሆናቸው ተመልክቷል።

የልማት ሥራው ገንዘብን ብቻ ሳይሆን ዕውቀትን፣ ዲዛይንን፣ በቂ የሰው ኃይል እና ግብዓት እንደሚጠይቅ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚከናወኑ ሥራዎች ጥራት ያላቸው እና ዘላቂ መሆን እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

"የምናስበው ብልጽግና የአንዲትን ድሃ እናት ሕይወት ካልነካ ዋጋ የለውም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሀብት ፍሰቱ እያንዳንዱን ዜጋ የሚነካ እና የሁሉም ሕይወት የሚቀየርበት መሆን እንደሚገባው ገልጸዋል።

በመንግሥት፣ በግል እና በሕዝብ አጋርነት 1.5 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት የተገባው ቃል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተገለጸ ሲሆን፣ የዚህ ሥራ ውጤትም ከተሞቻችንን በመቀየር የዜጎችን የኑሮ ዘዬ እንደሚያሻሽል ተነግሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በብዙ መስኮች ተስፋ እንዳላት እና በሰፊው ሥራ ከቀጠልን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከሌሎች ሀገሮች ጋር መተካከል እንደሚቻል ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል።

በሜሮን ንብረት

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: