የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ከንግግር ወደ ተጨባጭ ተግባር እንዲሸጋገር ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች የምትገኘው ኢትዮጵያ የ32ኛው አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) አዘጋጅነትን ስትረከብ ይዛው የቀረበችው ዋነኛ ስንቅ በተግባር የተፈተነውን የአረንጓዴ ዐሻራ ታሪካዊ ድል ነው።
ዓለም በአስቸጋሪ የአየር ንብረት መዛባት እየተፈተነች ባለችበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ ተግባራዊ እርምጃን በመውሰድ ለአፍሪካ ብሎም ለተቀረው ዓለም ትልቅ አብነት መሆን ችላለች።
በቱርክዬ በተካሄደው የኮፕ 31 ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳረጋገጡት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የዜጎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ የሚያሻሽል፣ የመቋቋም አቅምን የሚያጠናክር እና የልማት ስኬቶችን ዘላቂ የሚያደርግ ወሳኝ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሆኖ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ሆኗል።
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2027 በአዲስ አበባ በምታስተናግደው 32ኛው መድረክ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የምታቀርበው ይህ ተሞክሮ በአንድ ጀምበር የተገኘ ሳይሆን፣ ባለፉት ስምንት ዓመታት በተገነባ ጽኑ ራዕይ የመጣ ነው።
በመደመር ፍልስፍና እየተመራ በ2011 ዓ.ም "በአንድ ሰው 40 ችግኝ" በሚል ጥሪ የተጀመረው ይህ ንቅናቄ፣ ኢትዮጵያን ለኮፕ 32 መሪነት ያበቃ ታሪካዊ ምዕራፍ ከፍቷል።
ጉዞውም በ2012 ዓ.ም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት እንኳን ሳይቋረጥ "እየተጠነቀቅን እንተክላለን"፣ በ2013 ዓ.ም "ኢትዮጵያን እናልብስ"፣ በ2014 ዓ.ም "አሻራችን ለትውልዳችን"፣ በ2015 ዓ.ም "ነገን ዛሬ እንትከል"፣ በ2016 ዓ.ም "የምትተክል ሀገር የሚያጸና ትውልድ" እንዲሁም በ2017 ዓ.ም "በመትከል ማንሰራራት" በሚሉ መሪ ሐሳቦች ተፈጥሮን በማከም ኢኮኖሚን ማንሰራራት እንደሚቻል አስመስክሯል።
የ2018 ዓ.ም መሪ መልዕክት የሆነው "ተስፋን እንትከል" ደግሞ አረንጓዴ ዐሻራ የትውልድን ብሩህ ተስፋ እና የተፈጥሮን ሚዛን የመጠበቅ ዘርፈ ብዙ ጸጋ መሆኑን አረጋግጧል።
ወጣቶች፣ አዛውንቶች፣ ተማሪዎች፣ ሠራተኞች እና ባለሀብቶች በየዓመቱ ክረምት ሲገባ በጉጉት የሚጠብቁት ሕዝባዊ ባህል የፈጠረው ይህ መርሐ ግብር፣ የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ ከማድረጉም በላይ ትኩረቱን ወደ ጥምር ደን እርሻ (አግሮ ፎረስትሪ) እና ለምግብነት ወደሚውሉ ዕፅዋት አሸጋግሯል።
በተለይም ከ4.5 ቢሊዮን በላይ እንደ አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ማንጎ፣ ቡና እና ፖም ያሉ የፍራፍሬ ችግኞች መተከላቸው የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ፣ ከ6.5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር እና የወጪ ንግድ ምርቶችን በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ የግብርና ምርታማነትን ያሳደገ ሲሆን፣ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ የኃይል ማመንጫዎችን ከደለል በመታደግ የኢኮኖሚ ዕድሜያቸውን የሚያራዝም ታላቅ ኢንቨስትመንት ሆኗል።
ከታዳሽ ኃይል ልማት እና ዘላቂ የከተማ ግንባታ ጋር ተዳምሮ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የሚደረገውን ሽግግር ያፋጠነው ይህ ተሞክሮ፣ ለአጣዳፊ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶች በራስ አቅም ጠንካራ መፍትሔ መስጠት እንደሚቻል ያስተማረ ነው።
ይህንኑ የመፈጸም አቅም እና ሀገራዊ ጽናት በመያዝ ነው ኢትዮጵያ የኮፕ 32 ጉባኤን ስትረከብ ለአየር ንብረት ፋይናንስ አቅርቦት፣ ለጠንካራ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶች እና ተጋላጭ ለሆኑ ማኅበረሰቦች የመቋቋም አቅም ግንባታ ቅድሚያ ሰጥታ የምታራምደው።
በኮፕ 32 መድረክም የኢትዮጵያ ድምፅ እና ተሞክሮ ለዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ተግባራዊ እርምጃ ዋነኛ መሪ ሆኖ ይቀጥላል።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: