በመቐለ የተሃድሶ ሥልጠና የወሰዱ የቀድሞ ታጣቂዎች በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ባሉ የሥራ ዕድሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እንደሚሠሩ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር አቶ አወሉ አብዲ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ ይህን የገለጹት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር በመቐለ የተሃድሶ ሥልጠናቸውን ያጠናቀቁ የቀድሞ ታጣቂዎችን በጎበኙበት እና ከተሳታፊዎቹ ጋር በተወያዩበት ወቅት ነው።
ሚኒስትሩ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሥራ ጥያቄዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ይህም ለቀድሞ ታጣቂዎች እና ለወጣቶች በቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ምቹ ሁኔታ መኖሩን እንደሚያመለክት ገልጸዋል።
የሀገራችን የልማት ራዕይ እውን በማድረግ ኢትዮጵያ ጠንካራ፣ የምታመርት እና የምትከበር ሀገር እንድትሆን በመደመር መንግሥት እሳቤ እየተሠራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተስፋዓለም ይሕደጎ በፌዴራል መንግሥትና በብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አማካኝነት በትግራይ ክልል ዛሬ ሥልጠናቸውን ያጠናቀቁትን 7 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎች ጨምሮ ከ63 ሺህ 500 በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ሂደቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉ ለሥራ እና ለአቅም ግንባታ የሚውል 7.3 ቢሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን የጠቀሱት አቶ ተስፋዓለም፣ ለምግብ እና ለአልባሳት የሚውል 1.5 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በአጠቃላይ የፌዴራል መንግሥት ለተሃድሶ ሥራው 9 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉንም አስረድተዋል።
በአስማረ ብርሃኑ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: