Search

COP32 እና የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ለሀገራችን ልማትና ኢንቨስትመንት ያለው አበርክቶ

ሰኞ ኅዳር 07, 2019 123
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት የ32ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴን በመሰብሰብ አጠቃላይ የሥራ ሂደት መገምገማቸውን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ጉባኤው ለኢትዮጵያ ያለውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፣ COP32 ታላቅ ዓለም አቀፍ መድረክ ከመሆኑ ባለፈ ሀገራችን የአየር ንብረትና የአካባቢ ጥበቃ አጀንዳዎቿን የምታራምድበት፣ ዓለም አቀፍ አጋርነቷን የምታጠናክርበት፣ ኢንቨስትመንትን የምትስብበት እንዲሁም ብሔራዊ ጥረቶቿን ወደ ዘላቂ ውጤት የምትለውጥበት ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር አስገንዝበዋል። ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አገላለጽ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ውስጥ ያላትን ስትራቴጂያዊ ሚና የሚያመላክት ነው፡፡ ጉባኤው ለሀገራችን የሚያስገኛቸውን ዋና ዋና ዕድሎችም በአራት መሠረታዊ ነጥቦች ከፋፍሎ ማየት ይቻላል።
✅ ብሔራዊ የአየር ንብረት እና የአካባቢ ጥበቃ አጀንዳን ማራመድ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከልና የታዳሽ ኃይል አማራጮችን በተለይም የውኃ ኃይል ማመንጫዎችን በማስፋፋት የራሷን ተጨባጭ ተሞክሮ ገንብታለች። እንደ COP32 ያሉ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች እነዚህን ሀገር በቀል የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ለዓለም ለማስተዋወቅና ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ የያዘችውን የመሪነት ሚና ይበልጥ ለማጉላት ወሳኝ መድረክ ናቸው።
 
✅ ዓለም አቀፍ አጋርነትን እና ዲፕሎማሲን ማጠናከር የአየር ንብረት ለውጥ ድንበር ተሻጋሪ ችግር እንደመሆኑ መጠን የጋራ ትብብርን ይጠይቃል። በጉባኤው ላይ የሚደረጉ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ውይይቶች ኢትዮጵያ ከበለጸጉ ሀገራት፣ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና ከአካባቢ ጥበቃ ድርጅቶች ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታጠናክር ያስችላሉ። ይህም በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በአቅም ግንባታ እና በአየር ንብረት ፋይናንስ ድጋፍ ረገድ ሀገራችን ተጠቃሚ እንድትሆን በር ይከፍታል።
 
✅ የአረንጓዴ ኢንቨስትመንት ፍሰትን መሳብ ዘመናዊው የዓለም ኢኮኖሚ ወደ አረንጓዴና ዘላቂ ልማት እየተሸጋገረ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች ለአካባቢ ተስማሚ በሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎታቸው ጨምሯል። ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የታዳሽ ኃይል አቅም፣ ለአረንጓዴ ግብርና ምቹ የሆነ ሥነ-ምኅዳር እንዲሁም የካርቦን ንግድ ዕድሎችን በCOP32 መድረክ በተገቢው መንገድ በማቅረብ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ትልቅ ዕድል አላት።
 
✅ ብሔራዊ ጥረቶችን ወደ ዘላቂ ውጤት መለወጥ በሀገር ውስጥ የሚከናወኑ የአካባቢ ጥበቃና የልማት ሥራዎች ዘላቂነት እንዲኖራቸው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍና ዕውቅና አስፈላጊ ነው። ጉባኤው በሀገር ውስጥ የተጀመሩ የደን ልማት፣ የአፈርና ውኃ ጥበቃ እንዲሁም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የሚጣጣም ግብርና የመገንባት ጥረቶችን ከዓለም አቀፍ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፎች ጋር በማስተሳሰር ወደ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ውጤት ለመቀየር ያስችላል።
 
በመሆኑም COP32 ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስኬት መለኪያ ብቻ ሳይሆን፣ የጀመረችውን የአረንጓዴ ልማት ጉዞ ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የምታሸጋግርበት ስትራቴጂያዊ ምዕራፍ ተደርጎ ይወሰዳል። በአድማሱ አራጋው
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: