የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ እየተከናወኑ ባሉ ሰፊ የመልሶ ማልማት ሥራዎች የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እና የኑሮ ጥራት ማሻሻል ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል።
እነዚህ ሁለገብ የልማት እርምጃዎች የከተማዋን ነዋሪዎች ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ህይወት ከፍ የሚያደርጉ አዳዲስ መሠረተ ልማቶችን እውን እያደረጉ ናቸው። በተለይም በመልሶ ማልማት ማዕቀፍ ውስጥ እየተገነቡ ያሉ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች ከመኖሪያነት ባሻገር የሰው ልጅን ሰብዓዊ ክብር ሙሉ በሙሉ የሚመጥኑ ናቸው።
ለነዋሪዎች የተሠሩት ቤቶቹ ሻወር፣ ንጹህ ሽንት ቤት፣ የምግብ ማብሰያ ቤት እንዲሁም ምቹ የጋራ መናፈሻ ቦታዎችን ያካተቱ በመሆናቸው ለነዋሪዎች የተሟላና ጤናማ የመኖሪያ አካባቢን እየፈጠሩ ይገኛሉ።
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መውጫና መግቢያ መንገድ የሌላቸውን፣ ለሰው ልጅ ክብር የማይመጥኑ ደሳሳ ጎጆዎችን፣ ዳስ እና ሸራ ቤቶችን በማንሳት ነዋሪዎች በዘመናዊ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን መናገራቸው ይታወሳል።
እነዚህ በመልሶ ማልማት መርሐ ግብር የሚከናወኑ ሁለገብ የልማት ሥራዎች የከተማዋን ገጽታ በዘመናዊ መልኩ ከመቀየር ባለፈ፣ የሀገር ሀብት ለነዋሪዎች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲዳረስ እያደረጉ ናቸው።
የኑሮ ሁኔታዎችን በማሻሻል የነዋሪዎችን ማኅበራዊ ደኅንነት እና ንብረት ባለቤትነት የሚያረጋግጡ ሥራዎች መሠራታቸው የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋግጣል።
በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለው ይህ አጠቃላይ የመልሶ ማልማት ሂደት የነዋሪዎችን ህይወት እየለወጠ ሲሆን፣ የከተማ አስተዳደሩ በቀጣይነት እያካሄደ ያለው የልማት ራዕይ ዜጎች በክብርና በሰላም በከተማቸው ውስጥ የልማቱ ባለቤትና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል አበረታች ሥራ በመሆን ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በመሐመድ ፊጣሞ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: