ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመት የሚካሄደውን 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) በብቃት እና በስኬት የማስተናገድ ሙሉ አቅም እንዳላት በኢትዮጵያ የቱርክዬ እና የአውስትራሊያ አምባሳደሮች ገልጸዋል።
ዘንድሮ 31ኛው ምዕራፍ ላይ የደረሰው ዓመታዊው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP31) በቱርክዬ አንታሊያ እየተካሄደ ይገኛል።
ትናንት ጉባኤውን ለማስተናገድ ብርቱ ፉክክር ሲያደርጉ የነበሩት ቱርክዬ እና አውስትራሊያ፣ ዛሬ ለጉባኤው ስኬት በጋራ እየሠሩ ነው።
በዚህም ቱርክዬ ጉባኤውን በአንታሊያ ስታስተናግድ አውስትራሊያ በበኩሏ የሚደረጉ ድርድሮችን በፕሬዝዳንትነት እየመራች ትገኛለች።
ይህ ትብብር የዓለማችንን የአየር ንብረት ለውጥ ዳፋዎች ለመቋቋም በጋራ የመሥራትን አስፈላጊነት በተግባር ያረጋገጠ ሲሆን፣ በአውስትራሊያ የተደረጉ የቅድመ-ኮፕ ስብሰባዎችም ጉባኤው ከቃል ኪዳን ወደ ተግባራዊ እርምጃ እንዲሸጋገር መሠረት ጥለዋል።
በኢትዮጵያ የቱርክዬ አምባሳደር በርክ ባራን ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ የ31ኛው የአየር ንብረት ጉባኤ ስኬት የሚለካው የጋራ መግባባት በመፍጠር እና የተስማማንባቸውን ግቦች ወደ ተግባር በመለወጥ ብቃት መሆኑን ተናግረዋል።
"የ31ኛው ጉባኤ የአየር ንብረት እርምጃዎች አሁን ያሉትን ቃል ኪዳኖች ወደ ተጨባጭ አጋርነት፣ ኢንቨስትመንት እና ሊለካ ወደሚችል ተግባር መቀየር እንደሚቻል እንዲያሳዩ እንፈልጋለን፤ ለእኛ የጉባኤው ስኬት ማለት ሁሉም ተሳታፊዎች ከአንታሊያ ሲመለሱ በዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ሂደት እና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ላይ የላቀ አቅም ይዘው እንዲወጡ ማድረግ ነው። ምክንያቱም የትኛውም ሀገር በተናጠል የአየር ንብረት ችግሮችን መፍታት አይችልም" ብለዋል።
አክለውም የ32ኛው ጉባኤ መሳካት ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ቱርክዬ በጉባኤው ወቅትም ሆነ ከጉባኤው በኋላ ልምዷን ለኢትዮጵያ ማካፈሏን እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ አምባሳደር ፒተር ሀንተር (ዶ/ር) በበኩላቸው የትኛውም የአየር ንብረት ጉባኤ በተናጠል የሚቆም አለመሆኑን ጠቅሰው፣ የአሁኑ ጉባኤ በቅርቡ ኢትዮጵያ ወደምታስተናግደው 32ኛው ጉባኤ የሚሸጋገር ድልድይ መሆኑን አንስተዋል።
ከመቶ በላይ የድርድር አጀንዳዎች መቅረባቸውን የገለጹት አምባሳደሩ፣ አውስትራሊያ አባል ሀገራቱ በጋራ እንዲሠሩ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ላይ መሆኗንና ዝግጅቶችን ከማስተናገድ ጋር የተገኙ ልምዶችን ለማካፈል ከኢትዮጵያ መንግሥት አመራሮች ጋር በአጋርነት እየሠራች መሆኗን አስረድተዋል።
"ቀጣዩ ጉባኤ የአፍሪካ ጉባኤ ነው፤ ስለዚህ በአየር ንብረት ውይይቶች ውስጥ ጠንካራ የአፍሪካውያን ድምፅ እንዲሰማ ማድረግ ከሁሉም በላይ አስፈላጊ ነው" ሲሉ አጽንኦት የሰጡት አምባሳደር ፒተር ሀንተር (ዶ/ር)፣ የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት መገኛ የሆነችው እና ከኒውዮርክ እና ጄኔቫ ቀጥላ የዓለማችን ሦስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን የማስተናገድ ከፍተኛ ልምድ እንዳላት ጠቁመዋል።
ጉባኤው ኢትዮጵያ ከኃይል አቅርቦት ጀምሮ በአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲ ላይ ያላትን የመሪነት ሚና ለዓለም የምታስተዋውቅበት ወርቃማ ዕድል መሆኑንም አንስተዋል።
ዓለም ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ ሲያማትር እጇን አጣጥፋ መቀመጥን ያልመረጠችው ኢትዮጵያ፣ በሰጠችው ተግባራዊ ምላሽ ትናንት በተሳታፊነት ከምትሰየምበት መድረክ ዛሬ ወደ አስተናጋጅነት ተሸጋግራለች።
በአሁኑ ወቅትም በ31ኛው ጉባኤ ላይ ከወትሮው በተለየ በርካታ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችን ባካተተ ልዑክ ተወክላ በአንታሊያ የዝግጅት ልምድ እየወሰደች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ ከ90 በመቶ በላይ የኤሌክትሪክ ኃይሏን ከታዳሽ ምንጮች በማግኘት፣ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እና በዘላቂ የከተማ ልማት ያስመዘገበችውን ስኬት በማስፋት ጉባኤውን በላቀ ደረጃ ለማስተናገድ የተሟላ ዝግጅት እያደረገች መሆኗን በተደጋጋሚ አረጋግጣለች።
በሜሮን ንብረት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: